ቀጥታ፡

ከጥራት ደረጃ በታች ምርት የሚያመርቱ 14 ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22/2017(ኢዜአ)፦የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በ2017 በጀት ዓመ ት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ባደረገው የክትትል ስራ ከጥራት ደረጃ በታች ምርት የሚያመርቱ 14 ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ መውስዱን አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ ያላቸውን ምርቶች የሚያመርቱ 100 ፋብሪካዎች ላይ የኢንስፔክሽን ስራ ተሰርቷል።

በዚህም የ14 ፋብሪካ ምርቶች ከጥራት ደረጃ በታች ሆኖ በመገኘታቸው እርምጃ እንደተወሰደባቸው ተገልጿል።

እርምጃ የተወሰደባቸው ፋብሪካዎች የቆርቆሮ፣ የዕቃና የልብስ ሳሙናዎች፣ የአርማታ ብረት፣ ዱቄት ሳሙና፣ ዋየር፣ ፈሳሽ ሳሙና፣ ማከፋፈያ መሆናቸው ተመላክቷል።

በዚህም ድርጅቶቹ ከማምረት ሂደት እንዲታገዱ፣ ምርትን ወደ ገበያ እንዳያቀርቡ የማሸግ ስራ እንዲሁም ምርታቸውን ከገበያ ላይ እንዲሰበስቡና የማስተካከያ ስራዎችን እንዲሰሩ የሚያደርግ እርምጃ ተወስዷል።

በሩብ ዓመቱ ከደረጃ በታች በሆኑ 3 ሺህ ካርቶን የልብስ ሳሙና፣ 543 ፍሬ ፈሳሽ የዕቃ ማጠቢያ ሳሙናዎች፣ የአሌክትሪክ ገመዶች እና 2 ሺህ 683 ባለ 14 ዲያሜትር አርማታ ብረት ወደ ገበያ እንዳይወጣና እንዲወገድ መደረጉ ተገልጿል።

እንዲሁም 77 ሺህ 356 ሽንሽን ቆርቆሮ ምርት ወደ ገበያ እንዳይወጣ የማድረግ እና 760 ጥቅል የተለያየ መጠን ያላቸው የኤሌክትሪክ ገመድ ምርቶች ለገበያ እንዳይቀርቡና ከገበያ ላይ እንዲሰበሰቡ በማደረግ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል።

በዚህም ሸማቹ ጥራታቸውና ደህንነታቸው ካልተረጋገጡ ምርቶች በመከላከል የማህበረሰቡን ጤናና ደህንነት ማስጠበቅ መቻሉን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም