በሁለት ክልሎች ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሁለት ክልሎች ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 22/2017(ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚገኙ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ታሪኩ ኦቻ፤ በክልሉ ባህል፣ ታሪክና ሌሎች እሴት የሆኑ ኃብቶችን የመሰነድ፣ የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ክልሉ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ካስመዘገበቻቸው ዓለም አቀፍ ቅርሶች መካከል የኮንሶና የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ-ምድር ቅርሶች መገኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።
ክልሉ ተጨማሪ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዘገብ የተለያዩ ጥናትና ምርምር እያካሄደ መሆኑን ገልጸው፤ ለአብነትም የወላይታ ዘመን መለወጫ "ጊፋታ"ን ለማስመዝገብ የሚያስችል የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ ተካሂዶ መጠናቀቁን ገልፀዋል።
በተመሳሳይ የጋሞ ብሔረሰብ ሰላም መገለጫ የሆነው የ"ዱቡሻ" ሥርዓት እንዲሁም "የደራሼ ፊላ" ባህላዊ ሙዚቃ መሳሪያም በተመለከተም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የጥናትና ምርምር ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና ቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አክሊሉ ለማ ክልሉ በዓለም አቀፍ ቅርስነት ሊመዘገቡ የሚችሉ የተለያዩ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ባለቤት ነው ብለዋል።
ክልሉ በተለይም የጥንታዊና እድሜ ጠገብ ቤተ-እምነቶች፣ የድንጋይ ላይ ቅርሶች፣ የነገሥታት መቃብር መገኛ መሆኑንም ጠቅሰው፤ እነዚህን ቅርሶች የመሰብሰብና በሙዚየም የማደራጀት ሥራም ትኩረት መሰጠቱን ገልፀዋል።
ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከባህላዊ ቅርሶች በተጨማሪም በከፋና ሸካ ጥብቅ ደን የደመቀ፤ የተለያዩ ብርቅዬ አዕዋፋትና የዱር እንስሳት መኖሪያ የሆኑ ጨበራጩርጩራና ኦሞ ብሔራዊ ፓርክ መገኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ከቆይታ የተነሳ እየተበላሹ የሚገኙ ቅርሶችን መልሶ የመጠገን ሥራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ አክሊሉ፤ በ2016 በጀት ዓመት የአንዳራቻ መድኃኔዓለም፣ ፓሃ ጊዮርጊስና ቶንኮላ ቅርስ ጥገና ማካሄዳቸውን ለአብነት በመጥቀስ።
በተጓዳኝም፤ የዳውሮ ዘመን መለወጫ "ቶኪ ቤኣ"፣ የኮንታ ብሔረሰብ "ሂንጊጫ"፣ የካፊቾ ብሔረሰብ "ማሽቃሮ" የዘመን መለወጫ በዓላትን በማይዳሰሱ የዓለም ቅርስነት ውስጥ ለማካተት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይ የፈረንጆች ዓመት የወላይታ ሕዝብ ዘመን መለወጫ “ ጊፋታ” እና “ ሄር ኢሴ” የተሰኘ የኢሳ ባህላዊና አፋዊ የሕግ ሥርዓትን በዓለም በማይዳሰስ ወካይ ቅርስነት ለማስመዝገብ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን መግለጹ ይታወሳል።