የኢትዮጵያ የብሪክስ የከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የቴክኒክ ኮሚቴ አምስተኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የብሪክስ የከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የቴክኒክ ኮሚቴ አምስተኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሄደ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 22/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የብሪክስ የከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የቴክኒክ ኮሚቴ አምስተኛ መደበኛ ስብሰባውን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አካሂዷል።
ትላንት የተካሄደውን ውይይት የመሩት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ልዩ የፖሊሲ አማካሪ አምባሳደር ምኒልክ ዓለሙ ሲሆኑ በመድረኩ ከ24 የተለያዩ የአገራችን ተቋማት የተውጣጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
መድረኩ በሩስያ ካዛን የተካሄደው የ16ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ፣ ከኒውዮርክ የተ.መ.ድ ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን የተካሄደው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የካዛን የሼርፓዎች እና ምክትል ሼርፓዎች ስብስባ ውጤቶች ሪፖርት መቅረቡ ተገልጿል።
በመድረኮቹ የአገራችን ገንቢ ተሳትፎ ላይ ገለጻ መደረጉም እንዲሁ።
በቀረበው ገለጻ 16ኛው የብሪክስ ጉባዔ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ያስጠበቀ መሆኑንና ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ጉልህ ሚና እንድትጫወት ማስቻሉ በዝርዝር ቀርቧል።
በመሪዎቹ ጉባዔ የወጣው መግለጫ የአገራችንን ጥቅምና ፍላጎቶች ያስጠበቀ፣ አባል አገራቱ ለዓለም አቀፍ የፋይናንስ፣ የኢኮኖሚ እና የተ.መ.ድ. ጸጥታው ምክር ቤት መሻሻል እንዲሁም የታዳጊ አገሮች በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላቸው ሚና እንዲጨምር ቁርጠኝነታቸው የተገለጸበት ነው።
በስብሰባው ላይ በተደረገው ውይይት አገራችን በብሪክስ ማዕቀፍ በንቃት ለመሳተፍ እና በመድረኩ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅም ተቋማት ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው መወሰኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።