ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ 650 ትምህርት ቤቶች የከተማ ግብርናን ለተግባር ትምህርት እያዋሉት ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 22/2017(ኢዜአ):- በአዲስ አበባ 650 ትምህርት ቤቶች የከተማ ግብርናን ለተግባር ትምህርት እያዋሉት መሆኑን   የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ፋሩቅ ጀማል ፋሩቅ ጀማል ገለጹ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በመደበኛው ከግብርና ስራ በተጨማሪ የከተማ ግብርና ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባም በአትክልት እና ፍራፍሬ፣ በእንስሳት፣ በዶሮ እንዲሁም በንብ ማነብ ላይ ከግለሰብ እስከ ተቋማት ተሳትፎ እያደረጉ ናቸው።

በመዲናዋ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችም በግቢያቸው የሚገኙ ክፍት ቦታዎችን በጓሮ አትክልት እያለሙ ይገኛሉ።

የደጃዝማች ወንድይራድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የገላን የወንዶች አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የከተማ ግብርናን በመተግበር ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

ተማሪ ብሌን  ዓለሙ እና ተማሪ ረቂቅ ይልቃል በንድፈ-ኃሳብ የሚማሩትን የእርሻ ትምህርት በትምህርት ቤቱ የከተማ ግብርና  በተግባር ሙከራ በመፈተሽ የእውቀት አድማሳቸውን  እያሰፉ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የገላን ልዩ የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤተ ተማሪው ኤባ ዓለሙ በበኩሉ፥ በትምህርት ቤቱ የከተማ ግብርና መኖሩ ሳይንስን በተግባር በማረጋገጥ ስለ ግብርና በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ማድረጉን ጠቅሷል።

ተማሪዎቹ አክለውም ከትምህርት ቤት ውጪ በየአካባቢያቸው በጓሮ አትክልት እና በአረንጓዴ ልማት የመሳተፍ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዳመጡበትም ገልጸዋል።

የትምህርት ቤቶቹ ርዕሰ መምህራን እንዳሉት በትምህርት ቤቶች የከተማ ግብርና መጀመሩ በርካታ  ፋይዳ አለው ብለዋል።


 

የደጃዝማች ወንድይራድ ከፍተኛ ሁለተኛ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ካሱ ቱምሳ፥ ተማሪዎች   እያንዳንዱን አዝዕርትና ፍራፍሬ  ከብቅለት  ጀምሮ ለፍሬ እስኪበቃ የሚያልፍበትን ስነህይወታዊ ዑደት በአግባቡ እንዲያውቁ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።


 

የገላን ልዩ የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤት ርዕሰ-መምህር ካሳሁን መርጋ በበኩላቸው፥ የከተማ ግብርናው በትምህርት ቤት ደረጃ የማስተማር ስነዘዴን ተግባር ተኮር ከማድረጉ ባለፈ የስራ ባህልን መቀየሩን  ገልጸዋል።

ርዕሳነ መምህራኑ አክለውም የከተማ ግብርናው በተለይ በከተማ ያሉ ተማሪዎች የግብርና ሥራን እንዲያውቁ እንዲሁም እፅዋትን የመትከልና የመንከባከብ ባህል እንዲኖራቸው ማድረጉን ገልጸዋል።

በትምህርት ቤታቸው የከተማ ግብርናን እውን በማድረጋቸው ምርት ለሠራተኞችና ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ ማስቻሉንም አንስተዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ፋሩቅ ጀማል፤ ትምህርት ቤቶች በከተማ ግብርና ትግበራ ቀዳሚ መሆናቸውን አንስተዋል።

እስካሁን 650 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ወደ ልማቱ የገቡ ሲሆን፥ የምግብ ምርት ከማምረት ባለፈ ተማሪዎቻቸው ስለ እርሻ በተግባር የተደገፈ እውቀት እንዲይዙ በማድረግ እየተጠቀሙበት ነው ብለዋል።

በቀጣይም ሌሎች ትምህርት ቤቶች ተሞክሮውን ወስደው እንዲተገብሩና በመዲናዋ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንዲያግዙ፣ ራሳቸውም በገቢ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይሰራል ነው ያሉት።

ኮሚሽኑም ሙያዊ ስልጠና እና የግብዓት ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም