ዲጂታል ኢትዮጵያን በማፋጠን የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እየተሰራ ነው --- ኢትዮ ቴሌኮም - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢትዮጵያን በማፋጠን የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እየተሰራ ነው --- ኢትዮ ቴሌኮም
ሀዋሳ ፤ ጥቅምት 22/2017 (ኢዜአ):-ዲጂታል ኢትዮጵያን በማፋጠን ኢኮኖሚውን ለማሳደግ አዳዲስ የዘመኑን ቴክኖሎጂዎችን የማስገባትና የማስፋፋት ሥራ እየሰራ መሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ።
የአምስተኛው ትውልድ (5G) የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት በሀዋሳ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።
ትናንት ማምሻውን በተከናወነው የማስጀመሪያ ሥነስርዓት ላይ የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ አምስተኛ ትውልድ (5G) የሞባይል ኔትዎርክ አገልግሎት ዓለም የደረሰችበት የመጨረሻው ፈጣኑ የሞባይል ኔትዎርክ አገልግሎት መሆኑን ተናግረዋል።
በዓለም ላይ ካሉ ሀገራት ፈጣን የሚባለውን አምስተኛ ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት ተግባራዊ ያደረጉ የተወሰኑት ብቻ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
"ኢትዮጵያ ከእነዚህ ሀገራት አንዷ ናት" ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ከአዲስ አበባ ውጪ በሁሉም የክልል ከተሞች አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአምስተኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ የንግድ ስርዓቱን ለማሳለጥ፣ የግብርና ሥራን ለማዘመንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ሚናው የጎላ መሆኑንም አስረድተዋል።
"ባለፉት ስድስት ዓመታት ኩባንያችን በርካታ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገራችን በማምጣት ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል" ሲሉም ተናግረዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገለጻ፣ በአራተኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎትም አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ ከ424 በላይ ከተሞች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
ኩባንያው ላለፉት 130 ዓመታት ለሀገር የተሻሻለ ቴክኖሎጂዎችን በማምጣት ለመንግስት፣ ለማህበረሰቡ እና ለንግድ እንቅስቃሴው ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንና ራሱንም እያጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።
“የግብርና፣ የማዕድን፣ የትምህርት፣ የጤናና የአገልግሎት ዘርፎችን የመረጃ ልውውጥ በማሳደግ ዲጂታል ኢኮኖሚን በማስፋፋት በኩል ቴክኖሎጂው ጉልህ ሚና ይጫወታል” ብለዋል።
ኩባንያው ዲጂታል ኢትዮጵያን በማፋጠን ለአዳዲስ ሥራ ዕድል ፈጠራና በቴክኖሎጂ የታገዘ ንግድ በማካሄድ ተጨማሪ ሀብት ለማፍራት የሚቻልበት ዕድል እየፈጠረ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኩባንያው በተያዘው ዓመት 15 ከተሞችን በአምስተኛው ትውልድ (5G) የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት ለማስጀመር አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ኢትዮ ቴሌኮም ዓለም በደረሰበት ዲጂታል ቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ ሀገር እና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ እያበረከተ ያለው አስተዋጾ ከፍተኛ መሆኑን ነው የገለጹት።
ቴክኖሎጂው እንደ ሲዳማ ክልል የሚከናወኑ ተግባራትን ለማቀላጠፍና የሃዋሳ ከተማን ስማርት ሲቲ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
ወደክልሉ የመጣውን ቴክኖሎጂ በአግባቡ ተቀብለን ብዙ መስራትና መጠቀም ይገባናል ሲሉም ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂው ሥራዎች ቀልጣፋና ዘመናዊ የሚያደርግና የህዝቡንም ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል በመሆኑ በአግባቡ ጥቅም ላይ ልናውለው ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም አምስተኛው ትውልድ (5G) የሞባይል ኔትዎርክ አገልግሎትን ቀደም ሲል በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በድሬዳዋ፣ በሐረር፣ በጂግጂጋ እና በባሕር ዳር ከተሞች ማስጀመሩ ይታወሳል።
በኔትወርክ ማስጀመሪያ ሥነስርዓቱ ላይ የኢትዮ ቴሌኮም እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።