ቀጥታ፡

የምክክር ሂደቱ የቆዩ ችግሮችን ለመፍታትና አብሮነትን ለማጠናከር ወሳኝ ሚና ይጫወታል - ኮሚሽኑ 

ሶዶ፤ ጥቅምት 22/2017 (ኢዜአ):- የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ተቀራርቦ የመነጋገር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ የቆዩ ችግሮችን ለመፍታትና አብሮነትን ለማጠናከር ጉልህ አበርክቶ እንዳለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ተገኘወርቅ ጌቱ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኮሚሽኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በወላይታ ሶዶ እየመከረ ይገኛል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ተገኘወርቅ ጌቱ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያዊያን ችግሮቻቸውን በሰከነ መንገድ በውይይት ለመፍታት እያደረጉ ያሉት ተሳትፎና ጥረት የሚያስደስት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን በዘመናት መካከል የተገነቡ የአብሮነት፣ የመተሳሰብና የመከባበር ጠንካራ ባህል ያላቸው ቢሆንም በየጊዜው ተፈጥረው በነበሩ አለመግባባቶች እሴቶቹ እየተሸረሸሩ መምጣታቸውን አንስተዋል።

ከዚህ ቀደም ተቀራርቦ የመወያየት እድሉ ባለመኖሩ ትንንሽ አለመግባባቶች እየሰፉና መልካቸውን እየቀየሩ ወደ ግጭት ማምራታቸውን ገልጸዋል።

አሁን ላይ ተቀራርቦ የመነጋገር ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮችን ለመፍታትና የአብሮነት እሴቶችን ይበልጥ ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ችግሮችን ተቀራርቦ የመነጋገር እድሉን ተጠቅመን ካጋጠሙን ችግሮች በዘላቂነት ለመወጣት ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት ማድረግ አለብን ነው ያሉት።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው ላለፉት ቀናት ከተለያዩ የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር የልየታ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግስት አስፈፃሚ አካላትና የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ወኪሎች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።

እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ጨምሮ የልዩ ልዩ ማህበራትና ተቋማት ወኪሎች ጋር ምክክሩ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

ተሳታፊዎቹ ከማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በመሆን ክልሉን በመወከል በሀገራዊ የምክክር መድረኩ የሚሳተፉ ተወካዮችን የሚመርጡ ሲሆን ያሰባሰቡትን አጀንዳም ለኮሚሽኑ እንደሚያስረክቡ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም