በትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ድጋፍ እያደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ድጋፍ እያደረጉ ነው
መቀሌ እና አክሱም፤ ጥቅምት 22/2017 (ኢዜአ):- በትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የደረሰውን ሰብል በመሰብሰብ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ አስታወቁ።
በአሁኑ ወቅት በአብዛኞቹ የክልሉ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት ትንበያ ያመለክታል፡፡
የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ፅጋብ አረጋ እንዳሉት፤ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በመተባበር የደረሰ ሰብልን የመሰብሰብ ዘመቻ እያከናወነ ነው።
የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት በጋንታ አፈሹም ወረዳ ድብላ ቀበሌ ገበሬ ማህበር የደረሱ ሰብሎችን እየሰበሰቡ እንደሚገኝ እና ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ ዲን ነጋሽ አረጋይ (ዶ/ር) በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የአጨዳ ዘመቻ በማድረግ አርሶ አደሮችን በማገዝ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ባደረገው ጥሪ መሰረት ዩኒቨርሲቲው ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ ፤ በአካባቢያቸው የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ አርሶ አደሮችን ለማገዝ የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በቀጣይ ሳምንት ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚገቡ ተማሪዎችን በማስተባበር የአጨዳ ዘመቻ እንደሚያከናውን እና የምርት ብክነት እንዳያጋጥምም የተቻለውን ርብርብ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ገብረ እየሱስ ብርሃነ ዩኒቨርሲቲው ከማዕከላዊ ዞን ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመተባበር የደረሱ ሰብሎች ለመሰብሰብ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞችና ተማሪዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ከፍተኛ ስጋት ያሉባቸው አካባቢዎች ድረስ በመሄድ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምስራቃዊ ዞን ጋንታ አፈሹም ወረዳ የድብላ ቀበሌ ሴት አርሶ አደር ንግስቲ በየነ የዓዲ ግራት ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሰብላቸው ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ ባደረጉላቸው ድጋፍ ምርታቸውን በወቅቱ መሰብሰብ መቻላቸውን ገልጸዋል።
በማዕከላዊ ዞን ላዕላይ ማይጨው ወረዳ የዱራ ቀበሌ አርሶ አደር በርሀ አለም በበኩላቸው በአካባቢያቸው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ ክረምት ሙሉ ጥሮ ግሮ ያገኘው ምርት እንዳይባክን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች እና ወጣቶች የአጨዳ ዘመቻ ድጋፍ ማድረጋቸው ይበል የሚያሰኝና ሊጠናከር የሚገባው ተግባር ነው ብለዋል።
በትግራይ ክልል በዘንድሮው የመኸር ወቅት ከለማው መሬት 20 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።