ከአፖስቶ ሀገረ ሰላምና ከአለታ ወንዶ በንሳ ዳዬ የሚወስደው የአስፓልት መንገድ መበላሸት ለተለያዩ ችግሮች ዳርጎናል--ቅሬታ አቅራቢዎች - ኢዜአ አማርኛ
ከአፖስቶ ሀገረ ሰላምና ከአለታ ወንዶ በንሳ ዳዬ የሚወስደው የአስፓልት መንገድ መበላሸት ለተለያዩ ችግሮች ዳርጎናል--ቅሬታ አቅራቢዎች

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 22/2017(ኢዜአ)፦ ፖስቶ ሀገረ ሰላምና ከአለታ ወንዶ በንሳ ዳዬ የሚወስደው የአስፓልት መንገድ መበላሸት ለተለያዩ ችግሮች እንደዳረጋቸው አሽከርካሪዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሻሸመኔ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ቅሬታውን ለመፍታት ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል ዕቅድ ነድፎ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
ከአፖስቶ ሃገረ ሰላምና በንሳ ዳዬ እንዲሁም ከአለታ ወንዶ ዲላ አስፓልት መንገድ ከፍተኛ የትራፊክ እንቅስቃሴ ያለበት ቢሆንም በክረምቱ ዝናብ በፍተኛ ሁኔታ ለብልሽት ተዳርጓል።
ለመንገዱ ተገቢ ጥገና ባለመደረጉ ለተለያዩ ችግሮች እየተዳረጉ መሆናቸውን አሽከርካሪዎች፣ ተሳፋሪዎችና የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ለኢዜአ ገልጸዋል።
ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል ከአዶላ ወዩ ወደአለታ ወንዶ ሲያሽከረክሩ የነበሩት አቶ የማነህ ገብረመድህን ለመንገዱ አስፈላጊው ጥገና ባለመደረጉ ለተሽከርካሪ ብልሽትና ለወጪ እየዳረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በገቢያቸው ላይ ተጽዕኖ ከማሳደር ባለፈ የሀገር ሀብት ላይ የራሱን ጫና እያሳደረ በመሆኑ ለመንገዱ ፈጣንና ተገቢ ጥገና እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ከበንሳ ዳዬ ወደ ሃዋሳ ሲጓዙ ያገኘናቸው ተሳፋሪ አቶ መንግስቱ መለሰ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የመንገዱ መበላሸትና ተገቢ ጥገና አለመደረጉ ህብረተሰቡን ለእንግልት ዳርጎታል።
የመንገዱ መበላሸት ተሽከርካሪዎችን በጎዞ ወቅት ለብልሽት ስለሚዳርግ ተሳፋሪው ለጊዜ ብክነትና ለወጪ እየተዳረገ በመሆኑን ፈጣን መፍትሄ ያስፈልጋል ብለዋል።
መንገዱ ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ያለው ቢሆንም ለብልሽት በመዳረጉ የትራፊክ አደጋና የተሳፋሪ እንግልት እያጋጠመን ነው" ያሉት ደግሞ የጠጢቻ ወረዳ ፖሊስ የትራፊክ ሥራ ሂደት አስተባባሪ ዋና ሳጅን ቡሻሻ ቡቼ ናቸው።
ለመንገዱ ብልሽት የሚሰጠው መፍትሄ ጊዜያዊ በመሆኑ ችግሩ በተደጋጋሚ እንደሚከሰት ገልጸው በተለይም ከአፖስቶ ሃገረ ሰላም የሚወስደው የአስፋልት መንገድ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
የሲዳማ ክልል መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ታምሩ ታፌ ከአፖስቶ ሃገረ ሰላምና በንሳ ዳዬ የሚወስደው የአስፓልት መንገድ በመበላሸቱ በህዝቡ ተደጋጋሚ ቅሬታ እየተነሳ መሆኑን ተናግረዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ሻሸመኔ ቅርንጫፍ ጋር በመቀናጀት የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም ሥራው በሚፈለገው ልክ አልፈጠነም ብለዋል።
መንገዱ ከህብረተሰቡ የእለት ተዕለት ኑሮና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሄና ተገቢ ትኩረት እንዲያገኝ ቢሮው ክትትሉን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሻሸመኔ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ኢንጂነር ቴዌድሮስ መኩሪያ በበኩላቸው "በህዝቡ ቅሬታ ለቀረበባቸው መንገዶች ጥገና ለማድረግ ሥራዎች ጀምረናል" ብለዋል።
ከአፖስቶ ሃገረ ሰላም ያለው የአስፓልት መንገድ ብልሽት ውስን ቢሆንም መልሶ መገንባት የሚያስችል ጥገና የሚፈልግ በመሆኑ ጨረታ ወጥቶ በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘላቂ ጥገና የሚያስፈልገውን ቦታ ቆርጦ መልሶ የመገንባት ሥራ እስኪጀመር ድረስ የትራንስፖርት ሂደቱ እንዳይቋረጥ የሚያግዝ ጊዜያዊ ጥገና መጀመሩንም ተናግረዋል።
ንገድ ላይ ያጋጠመውን ብልሽት ለመጠገን ባለፈው ዓመት ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ከክረምት ወራት ጋር ተያይዞ ሥራውን ፈጥኖ መጨረስ እንዳልተቻለ ጠቁመው፣ በቀጣይ የጥገና ሥራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
ጥገና ለሚያስፈልጋቸው ከአፖስቶ ሃገረ ሰላም፣ ከአለታ ወንዶ በንሳ ዳዬ እና ከአለታ ወንዶ ዲላን ጨምሮ ለአምስት የመንገድ ፕሮጀክቶ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙንም ኢንጂነር ቴዌድሮስ ተናግረዋል።
ሥራውን በፍጥነት ለመጀመር የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉንና የዝናብ ሁኔታ ሲስተካከል የጥገና ሥራውን በፍጥነት ጀምሮ ለማጠናቀቅ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።