በመኸር እርሻ ከለማው መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር ላይ የደረሰ ሰብል ምርት ተሰብስቧል - የግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በመኸር እርሻ ከለማው መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር ላይ የደረሰ ሰብል ምርት ተሰብስቧል - የግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 22/2017(ኢዜአ)፦ በ2016/17 መኸር እርሻ ከለማው መሬት ውስጥ እስካሁን 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር ላይ የደረሰ ሰብል ምርት መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ ወቅታዊ የግብርና መረጃዎችን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በመኸር እርሻው 20 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በአነስተኛ ይዞታ ባላቸው አርሶ አደሮች መልማቱን አስታውሰው በሰፋፊ እርሻም ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ውስጥም እስካሁን 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር ላይ ያለ ምርት መሰብሰቡን ተናግረዋል።
በመኸር እርሻው በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ 11 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታሩ በኩታገጠም ሲለማ የሜካናይዝድ እርሻው 25 በመቶ መድረሱንም ጠቁመዋል።
የመኸር እርሻው አፈጻጸም በሁሉም ዘርፍ የተሳካ እንደነበር ጠቁመው በማዳበሪያ አቅርቦት፣ በምርጥ ዘር እና በሜካናይዜሽን ስኬታማ እንደነበር አንስተዋል።
በአሁኑ ጊዜ ምርት በደረሰባቸው አካባቢዎች የሰብል ስብሰባ መጀመሩን ጠቁመው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ምርቱን እንዳያበላሽም በርብርብ መሰብሰብ እንዳለበት ገልጸዋል።
በዘንድሮው የመስኖ ስራ በአጠቃላይ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት መታቀዱን የገለጹት ሚኒስትሩ ከዚህ ውስጥ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታሩ በስንዴ የሚሸፈን ይሆናል ብለዋል።
እስካሁን በበጋ የመስኖ ስራ 850 ሺህ ሄክታር የመሬት ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው 505 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።
ለ2017/18 የምርት ዘመን የሚውል የ24 ሚሊዮን ኩንታል የማዳበሪያ ግዢ ሂደት መጀመሩን የገለጹት ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ አፈር ተስማሚ የሆኑ ማዳበሪያ ለማቅረብ ሂደቶች ተጀምረዋል ብለዋል።
ከምርጥ ዘር አቅርቦት አንጻርም በአጠቃላይ በዘንድሮው ዓመት 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ መታቀዱን አመለክተዋል።
ከሌማት ትሩፋት አኳያም ዘንድሮ 150 ሚሊዮን ጫጩቶችን ለማሰራጨት ዕቅድ ተይዞ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም እንዲሁ።