ዘንድሮ ካለማነው ሰብል የተዞሻለ ምርት እንጠብቃለን -- የቄለም ወለጋ ን አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ዘንድሮ ካለማነው ሰብል የተዞሻለ ምርት እንጠብቃለን -- የቄለም ወለጋ ን አርሶ አደሮች
ጊምቢ ፤ ጥቅምት 22/2017(ኢዜአ)፦የተሻሻሉ አሰራሮችና የግብርና ግብአት ተጠቅመን ካለማነው ሰብል የተሻለ ምርት እንጠብቃለን ሲሉ የቄለም ወለጋ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡
በዞኑ በ2016/17 ምርት ዘመን መኽር ወቅት ከ400 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መልማቱን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በቀሌም ወለጋ ዞን ሀዋ ገላን ወረዳ መቻራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ከድር ዘይኑ ለኢዜአ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም በዘልማድ ከሚያለሙት ሰብል የሚያገኙት ምርት አነስተኛ ነው።
ዘንድሮ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን በግብርና ባለሙያ ድጋፍና ክትትል በመታገዝ በኩታገጠም ማሳ ላይ በቆሎ መዝራታቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በመጠቀም መዝራታቸውን ጠቁመው አሁን ላይ ቡቃያው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝና በሄክታር ከ50 አስከ 60 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ አመላክተዋል ።
ሌላው የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር አብዲ ኑር በበኩላቸው በ2016/17 ምርት ዘመን በመኽር ወቅት በግብርና ባለሙያ ምክር በመታገዝ ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ በዘር መሸፈናቸውን ተናግረዋል።
ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ተጠቅመው የዘሩት የበቆሎ ሰብል በአረምና ተባይ አንዳይጠቃ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን የማሳ ቁጥጥር ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል ።
በአንድ ሄክታር መሬት ከሚያለሙት በቆሎ ከ30 ኩንታል ያልበለጠ ምርት ያገኙ እንደነበር አስታውሰው ዘንድሮ በእጥፍ ብልጫ ያለው ምርት እንደሚጠብቁ አመላክተዋል።
ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ተጠቅመው የዘሩት የበቆሎ ቡቃያ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የዳሌ ሳዲ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር በጂጋ ኬነሳ ናቸው።
የቄለም ወለጋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ደረጄ ቄና፣ በዞኑ በ2016/17 ምርት ዘመን ከ400 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መልማቱን ተናግረዋል።
ከለማው መሬት ከ12 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።
በምርት ወቅቱ ሩዝ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ቦሎቄ፣ ባቄላና ሰሊጥ የለሙ ዋና ዋና የሰብል አይነቶች መሆናቸውን አመልክተዋል ።