ተምሮ ሀገርን የማገልገል ራዕይ ያነገቡት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ተምሮ ሀገርን የማገልገል ራዕይ ያነገቡት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በ2016 ዓ.ም በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ላስመዘገቡ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ሽልማት አበርክቷል።
ከተሸላሚ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች መካከል ማየት የተሳነው ሶፎኒያስ አንዱዓለም ትውልድና ዕድገቱ አዲስ አበባ ሲሆን፥ ትምህርቱን የተከታተለው በመዲናዋ ነው።
ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በሕዳሴ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በለቡ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል።
በ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የመልቀቂያ ፈተናንም ከ500ው 305 በማስመዝገብ ወደከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግባት የሚያስችለውን ከፍተኛ ውጤት አምጥቷል።
የትምህርት ቤት ጓደኞቹ የሚያደርጉለት የድምጽ ንባብ፣ የመምህራን ድጋፍና ጠንክሮ የማንበብ ባህልን ማጎልበቱ ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ያበቁት መሰረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጿል።
ተማሪ ሶፎኒያስ መምህር የመሆን ህልም እንዳለው ገልፆ፥ ለዚህም በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንደሚከታተል ነግሮናል።
ጠንክሮ በመማር ከፍተኛ ውጤት ለማምጣትና ሌሎችን ለማገዝ ማቀዱንም ነው የጠቀሰው።
ሌላኛው ተሸላሚ አካል ጉዳተኛ ተማሪ ሚካኤል ወልደማርያም በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና 288 ነጥብ በማስመዝገብ ለከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ማስመዝገቡን ይናገራል።
ለ12 ዓመታት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ሲከታተል የቆየው ተማሪ ሚካኤል የሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ትምህርቱን በአቃቂ አድቪንቲስት ትምህርት ቤት በመከታተል ወደከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተቀላቅሏል።
ቤተሰቡና ማህበረሰቡ በሚሰጡት የሞራል ስንቅና ጊዜውን በአግባቡ ለጥናት በማዋል የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡን አንስቷል።
በቀጣይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚኖረው ቆይታ በኪነ-ጥበብና በታሪክ ትምህርት በመከታተል ሀገሩን ወገኑን የማገልግል ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ገነት ቅጣው፤ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎቹ አሁን ለደረሱበት ደረጃ ትልቅ ሚና ሲጫወቱ ለነበሩ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የአካል ጉዳተኞችን በመማር ማስተማር ሂደት በማበረታታት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክተር ዲናኦል ጫላ፤ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከሚደረገው ጥረት በተጓዳኝ የአካል ጉዳተኞችን የትምህርት ተጠቃሚነት ለማጎልበት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የሴቶች፣ ህፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በቀጥታና በሪሜዲያል ፈተና የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ላስመዘገቡ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ፣ የአልባሳትና የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል።