በአማራ ክልል ሰላምን በማፅናት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው

ባህር ዳር፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ህግ የማስከበርና ሰላምን የማፅናቱ ተግባር በማስቀጠል ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።

"ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም" በሚል መሪ ሀሳብ  ህዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።

በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት  የፖለቲካና ርእዮተ አለም ዘርፍ ሃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤  በክልሉ  በነበረው ችግር ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት አድርሷል።

ሰላም የልማትም ሆነ ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ አንስተው፤ መንግስት ይህንን በመገንዘብ  ህግ የማስከበሩን ተግባር በማስቀጠል ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን አውስተዋል።

በዚህም ተስፋ ሰጭ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው፤ አሁንም ህዝቡን ባሳተፈ መንገድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በክልሉ  ችግሮችን ለመፍታትም በየአካባቢው ህዝባዊ መድረኮችን በማዘጋጀት ውይይቶች እየተካሄዱ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።


 

የኮንፈረንሱ ዓላማም  ችግሮችን  በመለየትና የተወሰዱ መፍትሄዎች ላይ በጥልቀት በመገምገም የተጀመረው የህግ ማስከበር ስራን አጠናክሮ በማስቀጠል በክልሉን ዘላቂ ሰላም ለማጎናጸፍ እንደሆነ አስረድተዋል።

የህግ ማስከበር ስራውን በህዝብ ተሳትፎ ዳር ለማድረስ ብሎም ሰላምን ለማስፈንና የተጀመሩ  የልማት ስራዎችን  አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል እንደሆንም ገልጸዋል።

በጥላቻ ላይ የተመሰረተውን የፅንፈኝነት አስተሳሰብን በማጥራት  ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች የሰከነ ውይይት በማካሄድ የተሰማቸውን ሃሳብና አስተያየት በማውጣትና በመምከር ለቀጣይ አቅጣጫ ጠቃሚ የሆነ ሃሳብ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በመድረኩት የመንግስትና የልማት ድርጅቶች ተቋማት ሃላፊዎች እንዲሁም ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም