በዞኑ ከ400 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ለሚገነባው የአለታ ወንዶ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ከ400 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ለሚገነባው የአለታ ወንዶ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ

አለታ ወንዶ ፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡- በደቡባዊ ሲዳማ ዞን ከ400 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ለሚገነባው የአለታ ወንዶ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ።
ፕሮጀክቱ 50 ሺህ የከተማዋን ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተመላክቷል።
የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እና የውሀና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አስፋው ዲንጋሞ (ዶ/ር) ናቸው።
በዚህ ወቅት የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር ከበደ ጋኖሌ እንደገለጹት፣ የውሀ ፕሮጀክቱ ግንባታ የሚከናወነው በክልሉ መንግስት እና በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ትብብር እንዲሁም በማቺንግ ፈንድ ድጋፍ ነው።
የንጹህ መጠጥ ውሃ የአካባቢው ነዋሪዎች የረጅም ጊዜ ጥያቄ እንደነበር ገልጸው፣ "ለእዚህ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን ፕሮጀክቱ ግንባታ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዷል" ብለዋል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ ስድስት የውሀ ማከፋፈያ ቦኖዎችን ጨምሮ የውስጥ ለውስጥ የውሀ ባንቧ መስመር ዝርጋታ፣ የውሀ ማከማቻ ጋንና ሌሎችንም ተጓዳኝ ሥራዎች እንደሚያካትትም አስረድተዋል።
እንደ ኢንጂነር ከበደ ገለጻ የውሃ ፕሮጀክቱ 50 ሺህ የከተማዋን ነዋሪዎች የንፁህ መጠጥ ውሀ ተጠቃሚ ያደርጋል።
የውሀና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አስፋው ዲንጋሞ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ሚኒስቴሩ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።
የውሃ ፕሮጀክቱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ሊፈጅ እንደሚችልም ነው ያመለከቱት።
የልማት አጋሮችን በማስተባበር ፕሮጀክቱን ስኬታማ ለማደርግና በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራልም ብለዋል።
በስነ ሥርአቱ ላይ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ በየነ በራሳን ጨምሮ ሌሎችም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና የአካባቢው ማህበረሰብ አካላት ተገኝተዋል።
በተጨማሪም የዓለም አቀፍ የልማት አጋር ተቋማት ተወካዮች መታደማቸው ታውቋል።