የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከመፍረስ የታደገ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡- የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከመፍረስ የታደገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በባንክና በኤምባሲ ስም የሚዘርፉ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ክትትል ተደርጎ እርምጃ እንደሚወሰድም አስጠንቅቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይህን ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር በተመለከተ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጡ ነው።

በዚሁ ጊዜ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከታደጋቸው ተቋማት ዋነኛው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆኑን አብራርተዋል።

ባንኩ በተለያዩ ምክንያቶች ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ገብቶ እንደነበር አስታውሰው፣ሪፎርሙ ባይመጣ ኖሮ ባንኩ ይፈርስ ነበር ብለዋል።

በኢኮኖሚ ሪፎርሙ ባንኩ የ900 ቢሊዮን ብር የተራዘመ ቦንድ እንዲያገኝ ማድረጉንም ነው የተናገሩት።

ባለፉት ዓመታት በተደረጉ የሪፎርም ስራዎች ባንኮች በሃብትም በቁጥርም ዕድገት አሳይተዋል ነው ያሉት።

በባንክና በኤምባሲ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች የውጭ ምንዛሬን በማሸሽ ህገ-ወጥ ተግባር እየፈጸሙ ነው ብለዋል።

እንዲህ አይነት ድርጊት ውስጥ የተሰማሩ አካላት ላይ ክትትል ተደርጎ እርምጃ እንደሚወሰድም አስጠንቅቀዋል፡፡

ባንክ በህጋዊ መንገድ የሚወዳደሩበት እንጂ በህገወጥ መንገድ በኮሚሽን ሃብት የሚሰበስቡበት መሆን የለበትም ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሃብት በመዝረፍ የውጭ ምንዛሬ ቢዝነስ ላይ የተሰማሩ አንዳንድ ኤምባሲዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ከድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከሆነ አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት።

የሪፎርሙ አንኳር ስራ ከሆኑት ውስጥ የውጭ ዕዳን ማቃለል መሆኑን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በተለይም ባለፉት ስድስር ዓመታት የውጭ ዕዳ ጫናው ከሀገራዊ ጥቅል ምርት አንጻር ከነበረበት 30 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 13 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ይህን አሃዝ በሚቀጥሉት ዓመታት ከአስር በታች ዝቅ በማድረግ ለትውልዱ ዕዳን ሳይሆን ምንዳን እናሸጋግራለን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም