በተለያዩ ዘርፎች እየታየ ያለው እመርታ የስራ ዕድል ለመፍጠር የተያዘው እቅድ እውን እንዲሆን ያስችላል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡- በተለያዩ ዘርፎች እየታየ ያለው እመርታ የስራ ዕድል ለመፍጠር የተያዘው እቅድ እውን እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር በተመለከተ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል በተያዘው በጀት ዓመት ሊፈጠር የታቀደው የስራ ዕድልና ወደ ተሟላ ትግበራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው ያስገኘው ውጤት ይጠቀሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ በ2017 በጀት ዓመት ለ4 ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎች የሀገር ውስጥና የውጭ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እቅድ ተይዟል።

ዕቅዱ ከፍተኛ አሃዝ ያለው በመሆኑ ለማሳካት በወር ለ350 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችል እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

በተለያዩ ዘርፎች እየተመዘገበ ያለው እመርታ እቅዱን ለማሳካት ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቁመዋል።

ግብርና 39 በመቶ፣ አገልግሎት 31 በመቶ እንዲሁም ኢንዱስትሪው 29 በመቶ የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሥራ ውል በመዋዋል በበጀት ዓመት ለ700 ሺህ ዜጎች የውጭ የሥራ እድል ለመፍጠር እቅድ መያዙን ገልጸው፤ ባለፉት ወራት 100 ሺህ ዜጎችን ለውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት መላካቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህም ባለፈ ሀገራቸው ላይ ሆነው ለተለያዩ ሀገራት የሚሰሩ 26 ሺህ ዜጎች የርቀት የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል።

መንግሥት ሥራ መቅጠር ብቻ ሳይሆን የሰለጠነ ባለሙያ ላይ ትኩረት ማድረጉን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማት ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችሉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው ገቢራዊ መደረጉ በተለይም የውጭ ምንዛሬ ግኝቱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱንም አብራርተዋል።

ለአብነትም ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

በሪፎርም ዘመኑ ለተለያዩ የልማት ስራዎች የሚውል ከ27 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ብድርና እርዳታ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም