በተጠባቂው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ መቻል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
በተጠባቂው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ መቻል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አሸነፈ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሃ ግብር መቻል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 1 ለ 0 አሸንፏል።
በድሬዳዋ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ በ79ኛው ደቂቃ የአማካይ ክፍል ተጫዋቹ አብዱልከሪም ወርቁ የግል አጨራረስ ብቃቱን ተጠቅሞ ያስቆጠራት ግብ መቻልን ባለድል አድርጋለች።
ውጤቱን ተከትሎ በገብረክርስቶስ ቢራራ የሚሰለጥነው መቻል በውድድር ዓመቱ ሶስተኛ ድሉን አስመዝግቧል። በ10 ነጥብ ከነበረበት አምስተኛ ደረጃ ወደ ሶስተኛ ከፍ ብሏል።
በአንጻሩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ሁለተኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል። ቡድኑ በአራት ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የውድድር ዓመት በ64 ነጥብ የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ ሌላኛው የዋንጫ ተፎካካሪ መቻል በ63 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ አይዘነጋም።
በሌላኛው የስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከመቀሌ 70 እንደርታ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።