ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያረጋግጡ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ላይ ከሁሉም ጋር በትብብር ትሰራለች - ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያረጋግጡ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ላይ ከሁሉም ጋር በትብብር እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) በአዲስ አበባ ከሚገኙ የዓለም አቀፍ ተቋማትና ኤምባሲዎች ተወካዮች ጋር ትውውቅ አድርገዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት ኢትዮጵያ ረጅም የመንግስት ታሪክ ያላት ጥንታዊት አፍሪካዊት ሀገር ናት።

ኢትዮጵያ በመርህ ላይ የተመሰረተ የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ በመከተል የነገን ብሩህ ተስፋ የሰነቀች ሀገር መሆኗንም አብራርተዋል።

በመሆኑም በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላትን የጎላ ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚና የወጣቶች ሀገር መሆኗን ገልጸው፣ እነዚህን እድሎች በመጠቀም ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማረጋገጥ በትብብር እንሰራለን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ማደግን መሰረት ያደረገ መርህ በመከተል በቀጣናው የመሪነት ሚናዋን እንደምትወጣም ተናግረዋል።

በኢጋድ ያላትን ስትራቴጂያዊ ሚና በብቃት መወጣቷን እንደምትቀጥል ገልጸው፣ ከዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት ጋር ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ያማከለ ግንኙነትን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

በአፍሪካ በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የንግድ፣ የቱሪዝምና የትራንስፖርት ትስስርን ለማሳደግ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያን ወደ ሙሉ ትግበራ ማስገባቷ ከሀገራት ጋር ያላትን የኢኮኖሚ አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚያስችልም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም