የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ለሀገሪቱ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ውጤታማነት እንደሚሰራ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ለሀገሪቱ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ውጤታማነት እንደሚሰራ ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ለሀገሪቱ የአምራች ዘርፍ መጠናከር የበኩሉን ሚና እንዲጫወት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለፀ።
የአዋሽ መልካሳ ኬሚካል ፋብሪካ ያለበትን የማምረት አቅምና የገበያ ትስስር በተመለከተ ከደንበኞቹ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር አውደ ጥናት አካሂዷል።
በአውደ ጥናቱ ፋብሪካው ሰልፈሪክ አሲድ፣ አሉሚኒየም ሰልፌትና ሀይድሮጂን ፐርኦክሳይድ ምርቶችን በበቂ መጠን እያመረተ ቢሆንም የገበያ ትስስር ችግር እንዳለ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የኬሚካል ክላስተር ፖርትፎሊዮ ዳይሬክተር ወይዘሮ ኢስማ ረዲ እንዳሉት የኬሚካል ኢንዱስትሪው ስትራቴጂክ የሆነና ለአምራች ኢንዱስትሪው ግብዓት የሚያመርት ነው።
የኬሚካል ዘርፉን ማሳደግ የሀገሪቱን እድገት የሚመሩ ኢንዱስትሪዎች የጀርባ አጥንት መደገፍ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ማቅረብ በርካታ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢንዱስትሪዎች ያለባቸውን የግብዓትና ሌሎች ችግሮችን በመፍታት በሀገር ውስጥ የምርት አቅርቦት እንዲኖር ማስቻሉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የኬሚካል ኢንዱስትሪው ለአምራች ዘርፍ መስፋፋት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሐድጉ ኃይለኪሮስ(ዶ/ር) በበኩላቸው አምራች ኢንዱስትሪውን መደገፍ ለኢንዱስትሪው ትራንስፎርሜሽን ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከአዋሽ መልካሳ ኬሚካል ፋብሪካ ጋር በተያያዘ የተነሱ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ፋብሪካው ለተለያዩ ፋብሪካዎች በግብዓትነት የሚያገለግሉ ኬሚካሎችን እያመረተ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የአዋሽ መልካሳ ኬሚካል ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ አህመድ ሞቱማ ናቸው።
ሆኖም በ2014 ዓ.ም በተለያዩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፋዊ ችግሮች ሳቢያ ለተጠቃሚዎች ምርት አለማቅረቡን ጠቅሰው፥ አሁን ላይ ወደ ምርት ቢገባም የገበያ ትስስር መፍጠር ላይ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።
የፋብሪካው ምርት ተጠቃሚ የሆኑት የኢትዮ ሌዘር የቆዳ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ጥላሁን ይሄይስና የአውዛ ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያ ተወካይ ከድሮ ዲኖ ፋብሪካው ምርቶችን እያቀረበላቸው ቢሆንም ጥራትን የጠበቀ ምርት ማቅረብ ላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል።