የባቡር ትራንስፖርቱ ለሀገር ሁለንተዊ ዕድገት እና የብልጽግና ጉዞ መሳካት የድርሻውን እንዲወጣ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢንጂነር ታከለ ኡማ

ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡- የባቡር ትራንስፖርቱ ለሀገር ሁለንተዊ ዕድገት እና የብልጽግና ጉዞ መሳካት የድርሻውን እንዲወጣ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለጹ።

የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት መሰረተ ልማትን ደህንነት መጠበቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በድሬዳዋ አስተዳደር ከሚገኙ ባህላዊ የማህበረሰብ መሪዎች ጋር ምክክር ዛሬ ተካሂዷል።

የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ እና ሌሎች የአመራር አባላት ከኡጋዞችና አባገዳዎች እንዲሁም ከአካባቢው ሽማግሌዎች ጋር በጉዳዩ ላይ መክረዋል።

ኢንጂነር ታከለ በወቅቱ እንደገለፁት፤ ከባህላዊ መሪዎችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር የተካሄደው ውይይት ፍሬያማ እና አስደሳች ነው።

የባቡር ትራንስፖርቱ ለሀገር ሁለንተዊ ዕድገት እና የብልጽግና ጉዞ መሳካት የድርሻውን እንዲወጣ መንግስት በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ከአዲስ አበባ ጅቡቲ እና ከጅቡቲ -ድሬዳዋ የዘመናዊ ባቡር የጭነት አገልግሎቶች ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቅሰው ይህም የባቡሩ መሠረተ ልማት በሚያልፍባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ እና አርብቶ አደሮችን ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።


 

የኢሳ፣ የአፍረንቀሎ እና የጉርጉራ ማህበረሰቦች ባህላዊ መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው የባቡሩ መሠረተ ልማት ለሀገር እና ለዜጎች ዕድገትና ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

ውይይቱም ይህን የሀገር ሃብትና ልማት በተሻለ ቅንጅት ደህንነቱ እንዲጠበቅ ኃላፊነታቸውን ይበልጥ እንዲወጡ መደላደል መፍጠሩን ገልጸዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ ለሚያነሳቸው የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች ልማቶች ምላሽ ለመስጠት አመራሮቹ ቃል መግባታቸው ያስደስታል ብለዋል።

ኡጋዝ ሙስጠፋ መሐመድ፣ አባገዳ አብዱረዛቅ አህመድ እና ኡጋዝ ዚያድ ዳውድ አክለውም የባቡር መስመሩ የሀገራችን የወጪና የገቢ ንግድና እንቅስቃሴዎች የሚሳለጥበት እና ለሀገር ከፍታ ወሳኝ ሚና የሚያበረክት መሆኑንም ገልጸዋል።

ባህላዊ መሪዎቹ የሚመሩትን ማህበረሰብ በማቀናጀት የባቡር መሠረተ ልማት ደህንነት እና እንቅስቃሴዎች በአስተማማኝ መንገድ የመጠበቁ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

መንግስት የባቡር መሠረተ ልማቱ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም