በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ ይጀምራል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡- በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ ይጀምራል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ፤ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚሁ ጊዜ፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት አዳዲስ ኃሳቦችን በማንሳት ወደ ተግባር መቀየርና ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን አብራርተዋል።

አሁን ላይ ሪፎርሞቻችንን ጨርሰን በታሪካችን አይተን የማናውቃቸው ውጤቶች ለትውልድ ሀገርን አፅንተን እንደምናስረክብ በተግባር አሳይተውናል ነው ያሉት።

የኢኮኖሚ ስብራቱን ለመጠገን በሁለት ዙር የተካሄደው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በተያዘው ዓመት ወደ ተሟላ ትግበራ መግባቱንም አመልክተዋል።

በተለያዩ ዘርፎች የተደረጉ የሪፎርም ሥራዎች በተያዘው ዓመት ማንሰራራት ይጀምራሉ ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎትና በቱሪዝም ዘርፎች የተመዘገቡ ውጤቶች የሪፎርሙን ማንሰራራት ማሳያ መሆናቸውን በመጥቀስ።

በተያዘው በጀት ዓመት አጠቃላይ የምጣኔ ኃብት ዕድገቱ 8 ነጥብ 4 በመቶ እንዲሆን መታቀዱንና ያለፉት ሦስት ወራት የዘርፎች አፈጻጸምም ከዕቅዱ በላይ እድገት ሊመዘገብ እንደሚችል ያመላከቱ ናቸው ብለዋል።

ከኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ በተለይም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች የበለጠ ጫና ውስጥ እንዳይገቡ መንግሥት ከፍተኛ ድጎማ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህም በዘንድሮ በጀት ከ300 እስከ 400 ቢሊየን ብር መንግሥት ለድጎማ መመደቡን ተናግረዋል።

ለነዳጅ፣ ለማዳበሪያ፣ መድኃኒትን ጨምሮ ለመሠረታዊ ሸቀጦች ከፍተኛ የበጀት ድጎማ መደረጉንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

ከደመወዝ ጭማሪ ጋር በተያያዘም 91 ቢሊየን ብር መመደቡን ጠቅሰው፤ ከጥቅምት ወር ጀምሮ የደመወዝ ጭማሪው ተግባራዊ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ ሰላምን ለማስፈን የመንግሥትን ቁርጠኝነት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ከኃይል ይልቅ ሰላም በእጅጉ አዋጭ መንገድ ነው ብለዋል።

መንግሥት ሕግንና ሥርዓትን የማስከበር ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም ከማንም በላይ ሰላም ይፈልጋል ነው ያሉት።

ጦርነት ምን ያህል እንደሚጎዳ በተግባር እናውቀዋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለኢትዮጵያ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ያለንን ህልም ለማሳካት ሰላምን በተጨባጭ ማሟላትም ወሳኝ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በኦሮሚያና አማራ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ፍላጎታቸውን በኃይል ለማሳካት ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር የሰላም ንግግር መጀመሩን ጠቅሰው፤ ሆኖም ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ሊያግዝ ይገባል ብለዋል።

የመገዳደልና ነገሮችን በኃይል ለማሳካት የሚደረግ ተግባር ኢትዮጵያን ለረዥም ጊዜ የጎዳ ስብራት በመሆኑ ሊበቃን ይገባል ነው ያሉት።

ኃሳብ አልባ ትግል ምንም ፍሬ የሌለው በመሆኑ፤ ወደ ሰላማዊ ንግግር በመምጣት በጋራ ለሀገር እድገት መትጋት ይበጃል ብለዋል።

መንግሥት ከለውጡ ጀምሮ የትኛውም አካል በሰላም አብሮ እንዲሰራ በተግባር እያሳየ መቀጠሉን ጠቅሰው፤ አሁንም የሚፈልገው ከየትኛውም ቡድን ጋር በሰላም መሥራት መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም