በስልጠናው በሙያችን ሀገርና ህዝብን ይበልጥ ማገልገል የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ ፈጥረናል - የመገናኛ ብዙኃን የስራ ኃላፊዎችና ሙያተኞች - ኢዜአ አማርኛ
በስልጠናው በሙያችን ሀገርና ህዝብን ይበልጥ ማገልገል የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ ፈጥረናል - የመገናኛ ብዙኃን የስራ ኃላፊዎችና ሙያተኞች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡- በስልጠናው በሙያችን ሀገርና ህዝብን ይበልጥ ማገልገል የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ ፈጥረናል ሲሉ የመገናኛ ብዙኃን የስራ ኃላፊዎችና ሙያተኞች ገለጹ።
"ሚዲያ ለብሔራዊ ትርክትና ሀገር ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ ለመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ባለሙያዎች ለሶስት ቀናት ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ተጠናቋል።
በሥልጠናው የትርክት እመርታ ከታሪካዊ ስብራት ወደ ሀገራዊ ምልዐት፤ እመርታ ከሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ወደ ብልጽግና እና የፖለቲካ እመርታ ከዴሞክራሲ መብት ወደ ሀገራዊ ኃላፊነት በሚሉ ርዕሶች ላይ የስልጠና ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ ስልጠናው የተያዘውን ሀገራዊ ራእይ ለማሳካት ለመገናኛ ብዙኃን ትልቅ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።
በስልጠናው የጋራ መግባባት እንደተፈጠረ ጠቅሰው፥ በዚህም የመገናኛ ብዙኃን አመራሮችና ሙያተኞች ለቀጣይ ስራዎቻቸው በቂ ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አብዱራህማን ሩቤ በስልጠናው የመገናኛ ብዙኃን ሀገርን የሚያሻግሩ ትርክቶች ላይ እንዲያተኩሩ የሚያደርግ አረዳድ መፈጠሩን ተናግረዋል።
እንዲሁም ኢትዮጵያ የያዘችውን የእድገት ጎዳና ማፋጠን የሚያስችል እውቀት የተገኘበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የአፋን ኦሮሞ መዝናኛ ክፍል ዋና አዘጋጅ ጫሊ ቱፋ በስልጠናው በፖለቲካና በኢኮኖሚ የተደረጉ ሪፎርሞች እና ትርክት ላይ በቂ እውቀት ማግኘቱን ተናግሯል።
በቀጣይም ለሚያከናውናቸው ስራዎች ትልቅ ስንቅ ያገኘበት መሆኑን በመጠቆም።
በመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የሚድያ ሞኒተሪንግ ክትትልና ድጋፍ መሪ ስራ አስፈጻሚ ካሳሁን መንግስቴ፥ አገልግሎቱ በተለያዩ ጊዜያት ለዘርፉ ባለሙያዎች የተለያዩ የአቅም ግንባታ መድረኮችን እያዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
ላለፉት ሶስት ቀናት የተሰጠው ስልጠና ባለሙያዎቹ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ተረድተው ለህብረተሰቡ የተሻሉ ስራዎችን እንዲያቀርቡ የሚያስችላቸው መሆኑን አመላክተዋል።
በዚህም ህብረተሰቡ መንግስት የሚያከናውናቸውን የልማት ስራዎች በመደገፍ ሚናውን አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደርጉ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል አቅም ፈጥሯል ነው ያሉት።
በቀጣይም መሰል ስልጠናዎች በስፋት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።