ቀጥታ፡

የክልሉ መንግስት ለህዝብ የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት ይሰራል -- አቶ እንዳሻው ጣሰው

ቡኢ፤ ጥቅምት 21/2017 (ኢዜአ)፡-የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ከህዝብ ለሚነሱ የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በምስራቅ ጉራጌ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ውጤትና ተግዳሮቶች ላይ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በቡኢ ከተማ መክረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የክልሉ መንግሥት በሁሉም አካባቢዎች የሚነሱ የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ ለማስቻል በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ነው።

ክልሉ ከተመሰረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ የውስጥ ሰላሙንና አንድነቱን በማጠናከር እንዲሁም ያሉትን የልማት አቅሞች በመለየት ረገድ ለውጦች ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል።

ክልሉ ያሉትን የልማት አማራጮች በተቀናጀ መንገድ ከተጠቀመ በቂ ሀብት እንዳለው አንስተው፤ በዚህ ረገድ የህዝብ የልማት ፍላጎቶችን ማስተናገድ በሚቻል መልኩ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይም ከፍትሐዊ የመሰረተ ልማት ተደራሽነትና ተጠቃሚነት እንዲሁም በግብርና ግብዓት አቅርቦት ረገድ በህዝብ ዘንድ የሚነሱ ጥያቄዎች መኖራቸውን አንስተው፤ መፍትሔ ላይ ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።

ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ አሰራሮች መተግበር ትኩረት የተሰጠው መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የክልሉ መንግስት ከህዝብ ጋር በቅርበት ችግሮችን እያዳመጠ የመፍትሄ ሐሳቦችን በጋራ እያፈለቀና እየተገበረ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

ይህን እያጠናከርን መሄድ ይገባናል ያሉት አቶ እንዳሻው፤ ህዝቡም የውስጥ ሰላሙንና አንድነቱን በማስቀጠል የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለስኬት ለማብቃት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በግብርናና ኢንቨስትመንት፣ በከተሞች ልማት እንዲሁም በትምህርትና ጤና ዘርፍም የሚከናወኑ ተግባራትና የሚመጡ ውጤቶችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሐሰን በበኩላቸው፣ ዞኑ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ያሉትን የልማት አማራጮች በመጠቀም ነዋሪውን ተጠቃሚ ለማድረግ ባደረገው ትጋት ውጤታማ መሆኑን አንስተዋል።

"ያሉንን ዕድሎች በአግባቡ ከተጠቀምን ከዚህ በላይ መልማትና መጠቀም እንችላለን" ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤በቀጣይም ተግዳሮቶችን በተቀናጀ መንገድ በመፍታት የበለጠ ለማሳካት እንሰራለን ብለዋል

አስተያየታቸውን ከሰጡት የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ዞኑ ከተመሰረተ ጀምሮ ህዝቡን በማስተባበር እያከናወናቸው ያሉ የልማት ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸው ዕገዛችንንም እናጠናክራለን ብለዋል።

ቄስ ሙሉጌታ ተሰራ መንግሥት የሚያከናውናቸው የሰላምና የልማት እንቅስቃሴዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ ይርጋለም ጌታቸው የሰላሙ ባለቤት እኛው በመሆናችን ሰላማችንን አጠናክረን ለማስቀጠል የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል።

በምክክር መድረኩ የክልልና የዞን የአመራር አካላት እንዲሁም ከዞኑ የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም