የትምህርት ጥራት ችግሮችን የሚፈቱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራት ችግሮችን የሚፈቱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ

ሮቤ፤ ጥቅምት 21 / 2017 (ኢዜአ)፡- የትምህርት ጥራት ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው ከሁለቱ የባሌ ዞኖችና ከሮቤ ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች፣ ርዕሳነ መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አህመድ ከሊል (ዶ/ር) እንዳሉት፣ዩኒቨርሲቲው መንግስት በትምህርት ዘርፍ ያጋጠመን የጥራት ችግር ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት እንዲሳካ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው።
የትምህርት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት፣ የትምህርት ሥርዓቱን የማሻሻል ስራዎች፣ የፈተና ሥርዓቱን የመቀየር ሂደት የጥረቱ ማሳያዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ይህንኑ መነሻ በማድረግ በአካባቢው ለሚገኙ የትምህርት ቤት መምህራንና አመራሮች የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በሚያግዙ ዘዴዎች ላይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በሁለቱ የባሌ ዞኖችና ከሮቤ ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ የትምህርት ባለድርሻ አካላት በዩኒቨርሲቲው እየተሰጠ ያለው የሦስት ቀን ሥልጠና የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለትምህርት ባለድርሻ አካላት በትምህርት ማስጠበቂያ ፓኬጆች ላይ ከሚሰጠው የአቅም ግንባታ ሥልጠና በተጓዳኝ የልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፍቶ ሥራ ማስጀመሩን አስታውቀዋል።
በዩኒቨርስቲው የምርምር ህትመትና የሥነ ምግባር ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር አዲሱ አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው በየደረጃው የሚገኙ መምህራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቆይታቸው በትምህርት ስብራት መንስኤና የመውጫ አቅጣጫዎች፣በትምህርት አመራር ጥበብ፣ በትምህርት ቴክኖሎጂና ሌሎች ተዛማጅ ዘርፎች ዙሪያ ግንዛቤ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።