የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከሁሉም ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከሁሉም  ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮችና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር በተመለከተ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ሰጥቶ መቀበልን መሰረተ ያደረገ መርህ ትከተላለች፡፡

ኢትዮጵያ ከራሷም አልፎ የአፍሪካ የብልጽግና ማዕከል መሆን የምትችል ታላቅ ሀገር መሆኗን መቀበል ይገባል ብለዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ ከቻይናም ከአሜሪካም ሆነ ከአውሮፓ ሀገራት ጋር በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላት ገልጸዋል፡፡

"እኛ የኢትዮጵያ ህልም ተሰላፊ ነን" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ከሚያግዙ ሀገራት ጋር እኩል ትብብር እንፈጥራለን፤ ለማንም የወገነ መርህ የለንም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ጋር ትከተለው የነበረው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የተሳሳተ እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር የሚያስችል ጠንካራ ትስስር መፍጠር አለብን ብለዋል፡፡

የመካከለኛው ምስራቅ በተለይም የአረብ ሀገራት ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላምና በትብብር የመልማት ፍላጎት እንዳላት ገልጸው፤ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ በማባላት መኖር አይቻልም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሱማሌን ግዛት ልትወስድ ተስማማች የሚል ትርክት ለመፍጠር ተሞክሮ እንደነበር ገልጸወል፡፡

የብሪክስ አባል ሆነን መቀላቀላችን ያለንን በትብብር የመልማት ፍላጎት ማስረዳት አስችሎናል ብለዋል፡፡

"መርከብ የሚሰምጠው በዙሪያው ባለው ውሀ መናወጽ ሳይሆን ውሀው መርከቡ ውስጥ ከገባ ብቻ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኛ ሀገራችንን ከክልል ከሰፈር ከፓርቲ ካስቀደምን ኢትዮጵያን ማንም ሊያንበረክክ አይችልም ብለዋል፡፡

በመሆኑም እንቃወማለን እንታገላለን የሚሉ ሰዎች ከጠላት ተልዕኮ በመቀበል መረጃ የሚሰጡ ወገኖች ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም