19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ነው - አቶ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡- 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የሀገርን መልካም ገጽታ በሚገነባና የኅበረብሔራዊ ፌዴራል ሥርዓቱን በሚያጸና መልኩ ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪ ኮሚቴና የማኔጅመንት አባላት የበዓሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ገምግመዋል፡፡

የግምገማ መድረኩን የመሩት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር የዘንድሮውን በዓል የሚያስተናግደው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብዙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በኅብርና በአብሮነት የሚኖሩበት በመሆኑ አከባበሩ ኅብረብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክርና ክልሉ ያለውን እምቅ ሀብት በሚያስተዋውቅ ደረጃ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡

አቶ አገኘሁ አክለውም በክልል ደረጃ የሚከበሩ የበዓል ዝግጅቶች በሕዝቦች መካከል ወዳጅነትንና አብሮነትን በሚያጠናክሩ የጋራ እሴቶች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ማስታወቃቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች አፈጻጸምን ለዐቢይ ኮሚቴ ያቀረቡት በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኙነት፣ የዴሞክራሲያዊ አንድነትና የሕገመንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ወይዘሮ ባንቺይርጋ መለሰ ናቸው፡፡

በሪፖርታቸውም በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች በዓሉን አስመልክቶ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።

የሕዝቦችን ዴሞክራሲያዊ አንድነት የሚያጠናክሩ፣ የልማት ሥራችን የሚያፋጥኑና የወል ትርክቶች በዜጎች ዘንድ እንዲሰርጹ የሚያደርጉ የአስተምህሮ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከበር ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም