በጎንደር ከተማ የልማት ፕሮጀክቶችን ከፍጻሜ ለማድረስ ህብረተሰቡ ለሰላሙ እያደረገ ያለውን አስተዋጾ ማጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ የልማት ፕሮጀክቶችን ከፍጻሜ ለማድረስ ህብረተሰቡ ለሰላሙ እያደረገ ያለውን አስተዋጾ ማጠናከር አለበት

ጎንደር/ሰቆጣ፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ከፍጻሜ ለማድረስ ህብረተሰቡ ለሰላሙ የሚያደርገውን አስተዋጾ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ገለጹ።
በጎንደርና በሰቆጣ ከተሞች "ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም!'' በሚል መሪ ሃሳብ ህዝባዊ ውይይት እየተካሄደ ነው።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በመድረኩ እንደገለጹት፤ ማህበረሰቡን በማሳተፍ የተከናወኑ የሠላም ግንባታ ሥራዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ሥራዎች በአግባቡ እንዲከናወኑ ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል።
በከተማው የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጀምሮ እየተፋጠነ መሆኑንም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቶቹን ከፍጻሜ በማብቃት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ህዝቡ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ሥራዎች ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
መድረኩ መላው የከተማው ህዝብ በሰላም ግንባታ ላይ መክሮ ሰላሙን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የድርሻውን እንዲወጣ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
"በተመሳሳይ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ህብረተሰቡ ለሰላም ዘብ ሆኖ መስራት አለበት" ያሉት ደግሞ የአስተዳደሩ ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃይሉ ግርማይ ናቸው።
በብሔረሰብ አስተዳደሩ ያለውን ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ጥምር ሃይሉ መስዋዕትነት መክፈላቸውን አመልክተዋል።
የህዝብን አጀንዳ አንግቢያለሁ በሚል ሽፋን የህዝብን ሃብትና ንብረት በመዝረፍ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ማድረስ ተገቢ እንዳልሆነም ተናግረዋል።
መንግስት የታጠቁ ቡድኖች ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ የሰላም ጥሪ ማቅረቡን አቶ ሀይሉ አስታውሰው፤ "ጥሪውን የተቀበሉ በርካታ ታጣቂዎች ወደቀደመ ሰላማዊ ኑሯቸው ተመልሰዋል" ብለዋል።
መንግስት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሰራ ያለውን ተግባር የታጠቁ ቡድኖችም እንዲያግዙ ህብረተሰቡ የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት አቶ ሃይሉ አሳስበዋል።
እርስ በርስ የሚከፋፍል አጀንዳ አንግበው ለሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ህብረተሰቡ ትኩረት ካለመስጠት ባለፈ በአንድነት ሊመክታቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በየመድረኮቹ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ነጋዴዎች፣ ሴቶች እና ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል።