ኢትዮጵያ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በቀይ ባህር ላይ የባህር በር ያስፈልጋታል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በቀይ ባህር ላይ የባህር በር ያስፈልጋታል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ፤ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም፥ የባህር በር ጥያቄን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም ኢትዮጵያ በባህር በር ጉዳይ ላይ ወደ ኋላ የማይል ይፋዊ አቋም እንዳላት ገልጸዋል።

ነገር ግን ይህን ለማሳካት ጦርነትም ሆነ የኃይል አማራጭ አንፈልግም ፍላጎታችንን ማሳካት የምንሻው በሰላማዊ አማራጭ ነው ብለዋል።፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምክንያታዊና ፍትሃዊ ጥያቄ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እኛ ባናሳካው ልጆቻችን ያሳኩታል ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ የትኛውንም ሀገር ላይ ወረራም ሆነ ጥቃት አትፈጽምም ብለዋል።

ነገር ግን ኢትዮጵያን ለመንካት የሚሞክሩ ካሉ አሳፍረን እንመልሳለን ይህን ማድረግ የሚያስችል በቂ አቅም አለን በማለት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም