የኮሪደር ልማት ማለት ኢትዮጵያን የሚመጥን ከተማ መገንባት ማለት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማት ማለት ኢትዮጵያን የሚመጥን ከተማ መገንባት ማለት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡- የኮሪደር ልማት ማለት ኢትዮጵያን የሚመጥን ከተማ መገንባት ማለት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ሰላምና ጸጥታ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያም የኮሪደር ልማት ማለት ኢትዮጵያን የሚመጥን ከተማ መገንባት ማለት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የኮሪደር ልማት ከከተሜነት እድገት ጋር የተሳሰረ ልማት ነው ብለዋል።
በኮሪደር ልማት ሰፋፊ መንገድ ከመስራት ባለፈ ታዳጊዎች እግር ኳስ የሚጫወቱባቸውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና የእግረኛ መንገዶች ተሰርተዋል ነው ያሉት፡፡
ይህም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሃዊ ልማት ለዜጎቻችን ያቀረብንበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ በተለያዩ ከተሞች ከምንሰራው የኮሪደር ልማት ባሻገር፤ የገጠር ኮሪደር ልማት ጀምረናል ነው ያሉት፡፡
ይህም ኢትዮጵያውያን የተሻለ ኑሮ ይገባቸዋል በሚል የተጀመረ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሟላ ብልጽግናን የምናረጋግጠውም በዚሁ መንገድ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡