በመደመር መንገድ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ገዥ ትርክት ወሳኝ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በመደመር መንገድ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ገዥ ትርክት ወሳኝ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡- በመደመር መንገድ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ገዥ ትርክት ወሳኝ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ፤ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም፤ የኢትዮጵያን ስብራት በሁሉም መልኩ ለመጠገን ከነጠላ ትርክት ይልቅ እንደ ሀገር የሚያሰባስብ ገዥ ትርክትን መገንባት ይገባል ብለዋል።
የዚህ ዋና ግቡ በመደመር መንገድ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ይህን ለማሳካት የትናንት ጠቃሚ ወረቶችን፣ የዛሬ ጊዜና አቅምን ለይቶ በአግባቡ መጠቀምና ተስፋ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጊዜ ጀምሯል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይህም ትልቅ ተስፋ እንደሆነ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ሲባልም ቤትና መኪና ብቻ እንዳልሆነ በመረዳት፤ በቁስም በመንፈስም በሞራልም ያደገ ማኅበረሰብ ያላት ሀገርን መገንባት ማለት ነው ብለዋል።
ድኅነትን የሚጠየፍ ሞራልን መገንባት እንደሚያስልግም በመጠቆም።
ገዥ ትርክት የሚገነባባቸው ውቅሮች ሕገ-መንግሥታዊነት፣ ኅብረ-ብሔራዊነት፣ ብልጽግናን እያረጋገጡ ድኅነትን እየደፈቁ መሄድ፣ ማረምና ማስቀጠል፣ ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር መሆናቸውን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያን ብልጽግናና ገዥ ትርክትን ማረጋገጥ ከአንድ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ከአንድ ትውልድ የሚሻገር ነው፤ እኛ መሰረቱን መጣል አለብን ብለዋል።
በመሆኑም በትምህርት፣ በኪነ-ጥብብ፣ በኃይማኖት ተቋማት፣ በሚዲያና ሌሎችም መንገዶች መሰረቱን መጣልና ማስረፅ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።