ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የብድር ጫና ከአጠቃላይ ሀገራዊ ጥቅል ምርት አንጻር 13 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የብድር ጫና ከአጠቃላይ ሀገራዊ ጥቅል ምርት አንጻር 13 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛ ዓመት ሶስተኛ መደበኛ ስብስባውን እያካሄደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ናቸው።

መንግስት የብድር ጫናን ለማቃለል የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ እና ባለፉት ስድስት ዓመታት ምንም አይነት የንግድ ብድር አለመውሰዱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የብድር ጫና ከአጠቃላይ ሀገራዊ ጥቅል ምርት አንጻር ከነበረበት ከ30 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 13 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

በሚቀጥሉት ዓመታትም ይህን አሃዝ ከ10 በመቶ በታች ዝቅ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት አየር መንገድና ቴሌን ሳይጨምር 13 ቢሊዮን ዶላር እዳ መከፈሉን ጠቅሰዋል።

ይህም እዳን ሳይሆን ለትውልዱ ምንዳን ለማውረስ የምናደርገውን ስራ የሚያግዝ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ባላፉት ሶስት ወራት በተለያየ መንገድ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር መምጣቱን ጠቁመው፥ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጭማሪ ማሳየቱን አመልክተዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ሃብት 400 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር አስታውሰዋል።

በአጠቃላይ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው 27 ቢሊዮን ዶላር ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገልጸዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በ6 ነጥብ 4 በመቶ ማደጉን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስተሩ፥በተለይ ለኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢ በመፍጠር ረገድ የተከናወኑ ስራዎችም ኢንቨስትመንት ለመሳብ ትልቅ አቅም መፍጠራቸውን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ያላት መሬትና ታዳሽ ኃይል፣እንዲሁም የሰው ሃይል ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንዳደረጋትና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውም የኢንቨስትመንት አቅምን ጥቅም ላይ ለማዋል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ባለፉት ሶስት ወራት ከወጪ ንግድ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱንና በዚህ አፈጻጸም ከቀጠለ በበጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ላይ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም