በክልሉ  ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ- አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) 

ደሴ፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ህብረተሰቡን ባሳተፈ አግባብ  ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በቅንጅት እየተከናወኑ እንደሚገኙ  የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለጹ።

 ''ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም'' በሚል መሪ ሃሳብ ህዝባዊ የውይይት መድረክ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) እንዳመለከቱት፤  በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ህብረተሰቡን በማስተባበር አበረታች ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል።

በቅንጅት በተከናወኑ ተግባራትም ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን  ጠቁመው፤ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የለውጥ ተግባራትም የበለጠ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ለዚህ ውጤታማነትም የክልሉን ተጨባጭ ሁኔታ ሁሉም ተገንዝቦ ለሰላም፣ ለልማትና ለሁለተናዊ ብልጽግና መተጋገዝ፣ መደጋገፍና በጋራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

''ከሁሉም ነገር በፊት ሰላም ያስፈልጋል'' ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ችግሮችን በውይይትና በንግግር መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

ህብረተሰቡ አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ ልማቱን መደገፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

የወልና የጋራ ትርክቶችን በማጎልበት ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ይኖርብናልም ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ተመሳሳይ ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም ከህብረተሰቡ ሀሳብ ግብዓት በመውሰድ ቀጣይ በተሻለ አግባብ እንሰራለንም ብለዋል።


 

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፤ ከህብረተሰቡ ጋር የከተማውን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰፋፊ ልማቶች ተሰርተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አውስተዋል።

በመድረኩ የክልልና የከተማ አመራር አባላት፣  የሐይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች ፣ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም