ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ 50 በመቶ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሀገር ውስጥ ባለኃብቶች እንዲያዙ በማድረግ በተኪ ምርት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ 50 በመቶ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሀገር ውስጥ ባለኃብቶች እንዲያዙ በማድረግ በተኪ ምርት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡- ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ 50 በመቶ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሀገር ውስጥ ባለኃብቶች እንዲያዙ በማድረግ በተኪ ምርት ከፍተኛ እመርታ መምጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ስብስባውን በማካሄድ ላይ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
በማብራሪያቸውም ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ዕድገት ባለፉት ዓመታት በተከናወኑት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሚጨበጥ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።
ከፍ ያሉ ምርት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ያላቸውን ችግሮች በመለየትና በማገዝ የምርት መጠኑን ከፍ እንዲያደርግ ጥረት መደረጉን ገልፀዋል።
ለአብነትም ከኤሌክትሪክ፣ ከቴሌኮሙኒኬሽን፣ ከባንክ፣ እንዲሁም ከመሬት አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ጨምሮ ሌሎችም መፈታታቸውን ተናግረዋል።
በሁሉም ሴክተር የኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ በሚያስችል ደረጃ ከላይ እስከ ታች በመተሳሰር መሥራት እንደሚገባ ጥረት መደረጉንም አንስተዋል።
በዚህ ዓመት ትላልቅ 72 ፕሮጀክቶች ወይንም ፋብሪካዎች ሥራ እንደሚጀምሩም ጠቁመዋል።
ከእነዚህ ውስጥ ዘጠኝ ጨርቃ ጨርቅ፣ 41 የምግብና መጠጥ ፕሮጀክቶች፣ አራት የኮንስትራክሸንና ኬሚካል ፕሮጀክቶች፣ 15 የቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ትልቅ ገበያ ሊያመጡ የሚችሉ ሦስት የሚሊተሪ ፋብሪካዎች በዚህ ዓመት ምርት እንደሚጀምሩ ገልጸዋል።
ከሪፎርሙ በኃላ በኢንዱስትሪ ፓርኮች 50 በመቶ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ 50 በመቶ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሀገር ውስጥ ባለኃብቶች እንዲያዙ በማድረግ በተኪ ምርትም ከፍተኛ እመርታ መምጣቱን ገልጸዋል።