2017 የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ የምንጀምርበት ዓመት ይሆናል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2017(ኢዜአ)፡-ከዚህ ዓመት ጀምሮ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እንጀምራለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ፤ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

በማብራሪያቸውም አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ማንሰራራት የምንጀምርበት ዓመት ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ሪፎርሞቻችንን ጨርሰን በታሪካችን አይተን የማናውቃቸው ውጤቶች እያየን ለትውልድ ሀገርን አፅንተን እንደምናስረክብ አሳይተውናል ነው ያሉት።

በሪፎርሙ ዓመታት የተቋማት የፖለቲካ የኢኮኖሚ ሥርዓቱን ሪፊርሙን የማካሄድና የማፍታታት ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

የኢኮኖሚ ሪፎርሙንም በዚህ ዓመት ወደ ተሟላ ትግበራ ማስገባት መቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህ ዓመት የማንሰራራት ዓመትን በመጀመር ወደ ማፅናት ምዕራፍ እንሸጋገራለን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያን የማፅናት ምዕራፍንም ትውልድ የሚያስቀጥለው ይሆናል ብለዋል።

ይህን ስንል ኃሳብ ብቻ ሳይሆን ባለፉት ዓመታት ሀሳቦችን በተግባር በሚለካ መልኩ እንዲለወጡና ውጤት እንዲያመጡ በማድረግ ማሳየት መቻሉን አንስተዋል።

ይህንን ውጤታማ በማድረግም የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዓመት በዚህ ዓመት እንጀምራለን ነው ያሉት።

በትናንት ለቅሶና በትናንት እሳቤ ያሉ ሰዎች ወደሚቀጥለው ምዕራፍ መሸጋገራችንን ሊያውቁ ይገባል ብለዋል።

የተጀመረው አዲስ ምዕራፍም በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ በሁሉም መስክ በሚቆጠር ውጤት እንደሚገለጥ  ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት ከታቀደው በላይ 8 ነጥብ 1 በመቶ እድገትመመዝገቡን አንስተው፥ በዚህ ዓመት 8 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ግብ መያዙን አመላክተዋል።

ያለፉት ሦስት ወራት የዘርፎች አፈጻጸምም ከእቅዱ በላይ እድገት ሊመዘገብ እንደሚችል ያሳያል ነው ያሉት።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም