የአምናዎቹ የዋንጫ ተፎካካሪዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቻል በሊጉ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአምናዎቹ የዋንጫ ተፎካካሪዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቻል በሊጉ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 21/2017 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቻል ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በድሬዳዋ ስታዲየም ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ደግሞ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር አምስት ግቦችን አስተናግዷል።
በአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ቡድን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ4 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የውድድር ዓመት በ64 ነጥብ የሊጉ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ማንሳቱ የሚታወስ ነው።
ተጋጣሚው መቻል በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
በአራቱ ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን ሲያስቆጥር አራት ጎሎችን አስተናግዷል። በገብረ ክርስቶስ ቢራራ የሚሰለጥነው መቻል በሰባት ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
አምና ለዋንጫ ሲፎካከር የነበረው መቻል በ63 ነጥብ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
በዛሬው ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከመቀሌ 70 እንደርታ ጋር ይጫወታሉ።
ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ቡናማዎቹ አራት ጎሎችን ሲያስቆጥሩ አምስት ግቦችን አስተናግደዋል።
በነጻነት ክብሬ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡና በአራት ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ተጋጣሚው መቀሌ 70 እንደርታ በበኩሉ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ድል ሲቀናው አንድ ጊዜ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
መቀሌ 70 እንደርታ በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር አምስት ጎሎችን አስተናግዷል። በዳንኤል ፀሐዬ የሚመራው ቡድን በስምንት ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ባህር ዳር ከተማ ሲዳማ ቡና 2 ለ 0 እንዲሁም ወላይታ ድቻ ሀዲያ ሆሳዕናን 1 ለ 0 አሸንፏል።