ወላይታ ድቻ በሊጉ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዘገበ 

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 20/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታ ወላይታ ድቻ ሀዲያ ሆሳዕናን 1 ለ 0 አሸንፏል።

ማምሻውን በድሬዳዋ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አጥቂው ካርሎስ ዳምጠው በ67ኛው ደቂቃ ለቡድኑ የማሸነፊያውን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ በሊጉ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል። በአጠቃላይ በውድድር ዓመቱ ያሸነፋቸውን ጨዋታዎች ብዛትም ወደ አራት ከፍ አድርጓል።
ወላይታ ድቻ በ12 ነጥብ ተመሳሳይ ነጥብ በያዘው ሲዳማ ቡና በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
በውድድር ዓመቱ ሶስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና በአራት ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ቀን ላይ በተደረገ የስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ባህር ዳር ከተማ ሲዳማ ቡናን 2 ለ 0 አሸንፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም