ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፉ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፉ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 20/2017(ኢዜአ)፦የግብርና ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፉ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝና ሌሎች አደጋዎችን ለመቆጣጠር የራሷ የኬሚካል ርጭት አውሮፕላኖች ስላልነበራት ከፍተኛ ወጪ ስታደርግ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይህንንም ከግምት በማስገባት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የአደጋ መቆጣጠሪያ የኬሚካል ርጭት አውሮፕላኖች እንዲኖራት አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ ዘመናዊ የኬሚካል ርጭት አገልግሎት የሚሰጡ አምስት ዘመናዊ ኤር ትራክተሮች ግዥ ተፈጽሞላቸው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወደ ሥራ መግባታቸው ይታወቃል።
አውሮፕላኖቹ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙና ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የመስጠት አቅም ያላቸው በመሆናቸው እንደ እሳት ያሉ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በፍጥነት ምላሽ መስጠት የሚችሉ መሆናቸውም ተጠቅሷል።
ከሰሞኑም በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን በሚገኘው የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ማሳዎች ላይ እነዚህን አምስት ዘመናዊ የርጭት አውሮፕላኖች (ኤር ትራክተርስ) በመጠቀም የጸረ አረምና የጸረ ተባይ የኬሚካል ርጭት ተካሂዷል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው መለሰ መኮንን (ዶ/ር)፤ የእነዚህን ዘመናዊ የርጭት አውሮፕላኖች (ኤር ትራክተርስ) በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፤የኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ እድገት ከሚፈታተኑ ችግሮች መካከል በወረርሽኝ መልክ ወይም ድንበር ዘለል በሆነ መልኩ የሚከሰቱ ተባዮችና አረሞች ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እነዚህም በተለያዩ ወቅቶች አገሪቱ በምታመርታው ልዩ ልዩ የእፅዋትና የሰብል ምርቶች ላይ አመርቂ ውጤት እንዳይመጣ ከማድረግ አንጻር ማነቆ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ሚኒስቴሩ የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የዳሰሳ ሥራ በመሥራት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ተግባር እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከእነዚህ መካከል ዘመናዊ የርጭት አውሮፕላኖች (ኤር ትራክተርስ) በመጠቀም የጸረ አረምና እንዲሁም የጸረ ተባይ የኬሚካል ርጭትን ጨምሮ ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የዘመናዊ የርጭት አውሮፕላኖች (ኤር ትራክተርስ) የግብርና ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ተግዳሮት የሚሆኑ ተባዮችን ብሎም አረሞችን ለመከላከል ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አንስተው ይህም በልዩ ትኩረት ይሰራበታል ብለዋል።