በክልሉ በሥራ ዕድል ፈጠራ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በሥራ ዕድል ፈጠራ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ

ቡኢ ፤ ጥቅምት 20/2017 (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሥራ ዕድል ፈጠራ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው አስታወቁ።
የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ዛሬ በምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡኢ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፣ ሁለንተናዊ ልማትን ማረጋገጥ የሚቻለው ወጣቶችን በሁሉም መስክ ማሳተፍና ተጠቃሚ ማድረግ ሲቻል ነው።
የክልሉ መንግስትም ለአዳዲስ የሥራ ዕድል ፈጠራ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ወጣቶችን ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የክልሉ ወጣቶችም ጊዜያቸውንና ያላቸውን እውቀት በአግባቡ ተጠቅመው ከራሳቸው ባለፈ የአካባቢያቸውን ህዝብ መጥቀም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ወጣቶች በተለያዩ የገቢ ማስገኛ መስኮች በመሰማራት ለውጤት መትጋት እንዳለባቸው ጠቁመው፣ የክልሉ መንግስት ለወጣቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው ብለዋል።
በክልሉ በበጀት ዓመቱ ከ350 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ መሆኑንም አቶ እንዳሻው ጠቁመዋል።
ከልማት ተጠቃሚ የሚሆነው ሰላምን በዘላቂነት ማጽናት ሲቻል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ወጣቶች አብሮነትን ለሚያጠናክሩ ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጡም አስገንዝበዋል።
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን በበኩላቸው እንዳሉት፣ በአካባቢው የህብረተሰቡን የሰላምና የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስተዳደሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።
ይህን ሥራ ለማጠናከርና የወጣቱን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መድረኩ ገንቢ ሚና እንደሚኖረውም አመልክተዋል።
እንደ አቶ ሙስጠፋ ገለጻ፣ በዞኑ በበጀት ዓመቱ ከ41 ሺህ በላይ ሥራ አጥ ወጣቶች ተለይተው እስካሁን ድረስ ለ3ሺህ 700 ወጣቶች የሥራ እድል ተፈጥሯል።
ይህም ከተለዩ ወጣቶች አንጻር ዝቅተኛ በመሆኑ በቀጣይ ወራቶች የተሻለ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ከምስራቅ መስቃን ወረዳ የመጣው ወጣት ውኢብ አበበ ለወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንቅፋት ለሆኑ ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቋል።
"እኛ ወጣቶች ፀረ ሰላም ኃይሎችን በመታገል የአካባቢያችንን ሰላም አጠናክረን ለማስቀጠል ትልቁን ኃላፊነት መውሰድ አለብን" ሲልም ገልጿል።
በክልሉ መንግስት ለወጣቶች በተመቻቸው የሥራ ዕድል ፈጠራ ሰርቶ ለመለወጥ ዝግጁነቱንም አረጋግጧል።
የዞኑ አስተዳደር የወጣት ሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ያለበትን ውስንነት እንዲፈታ የጠየቀችው ደግሞ ከመስቃን ወረዳ የመጣችው ወጣት ሮዛ አበራ ናት።
በተለይ ተደራጅተው ለሚመጡ ወጣቶች የማምረቻ እና የመሸጫ ቦታ በፍትሀዊነት በማቅረብ ወጣቶችን ማበረታታት ይገባል ብላለች።
የወጣቱን ትኩስ ጉልበትና እውቀት በመጠቀም የአካባቢውን ሁለንተናዊ ለውጥ ማፋጠን እንደሚገባም ተናግራለች።
በመድረኩ ላይ ከክልሉና ከምስራቅ ጉራጌ ዞን የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች እና ወጣቶች ተሳትፈዋል።