በርካታ የጃፓን ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢንቨስት ማድረግ ይፈልጋሉ-አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ - ኢዜአ አማርኛ
በርካታ የጃፓን ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢንቨስት ማድረግ ይፈልጋሉ-አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ
አዲስ አበባ፣ጥቅምት 20/2017 (ኢዜአ)፦በርካታ የጃፓን ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢንቨስት ማድረግ እንደሚፈልጉ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ተናገሩ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ከሆኑት ሺባታ ሂሮኖሪ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ወቅት፥ የኢትዮጵያ ታምርት ሃገራዊ ንቅናቄን እና አቅም ያላቸው አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ የዘርፉን ምርታማነት ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፥ ጃፓን የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን በጃፓን ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ኮይካ) በኩል እያደረገች ላለው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
ዘርፉን በመደገፍ ውጤታማና ተወዳዳሪ ማድረግ የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት በቀላሉ ማሳለጥ የሚያስችል በመሆኑ ድርጅቱ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡
አቶ መላኩ፥ ጃፓን ለአምራች ኢንዱስትሪ ዕድገት ዋና ማሳያ ሞዴል ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለአምራች ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት የተመቸ ፖሊሲና አሰራር ስርዓት እንዳላት ለአምባሳደሩ አስረድተዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም፥የጃፓን ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በዘርፉ እንዲሰማሩ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ በበኩላቸው በርካታ የጃፓን ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢንቨስት ማድረግ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
የጃፓን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ያላቸው ፍላጎት ወደ ተግባር እንዲቀየር እንደሚሰሩ አምባሳደር ሺባታ መናገራቸውን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡