የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት እና የልማት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ ውይይት በዋሺንግተን ዲሲ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት እና የልማት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ ውይይት በዋሺንግተን ዲሲ ተካሄደ
አዲስ አበባ ፤ጥቅምት 20/2017(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት እና የልማት አቅጣጫ አስመልክቶ የተዘጋጀ ውይይት በዋሺንግተን ዲሲ ተደርጓል።
ውይይቱን ያዘጋጀው ተቀማጭነቱን በዋሺንግተን ዲሲ ያደረገው የዓለም አቀፍ ጉዳዮች የምርምር ተቋም “Carnegie Endowment for International Peace” ነው።
ከዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ስብስባ ጎን ጎን በተካሄደው ውይይት ላይ የኢትዮጵያ ልዑክ ተሳትፎ አድርጓል።
የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች፣የባለሙያዎች ስብስብ (ቲንክ ታንክ)፣ የብዝሃ ወገን ተቋማት እና ምሁራን በምክክሩ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ የሪፎርም ስራ እስከ አሁን ያስገኛቸው ውጤቶች፣ያሉ ምቹ እድሎች እና ፈተናዎች እና ቀጣይ የትግበራ ሂደቱን አስመልክቶ ውይይት መደረጉን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።