ቀጥታ፡

ባለፉት ሶስት ወራት ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ከ 95 ሺህ ዩኒት በላይ ደም ተሰብስቧል

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 20/2017 (ኢዜአ)፦ባለፉት ሶስት ወራት ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ከ95 ሺህ ዩኒት በላይ ደም መሰብሰብ እንደተቻለ የኢትዮጵያ ደምና  ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ። 

የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሐብታሙ ታዬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አገልግሎቱ የበጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾችን ቁጥር ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት አገልግሎቱ 513 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ዕቅድ ይዞ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 100 ሺ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ በሶስት ወራት የዕቅዱን 95 ከመቶ በማሳካት ከበጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች ከ95 ሺህ ዩኒት በላይ ደም መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

ደም የሚለግሱ በጎ ፍቃደኞችን ቁጥር ለማሳደግ የሚያግዝ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በመስራት ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

ይህን ተከትሎ በትምህርት ቤቶች የደም ልገሳ ክበቦችን በማቋቋም ጭምር ተማሪዎች በበጎ ፍቃድ ተግባሩ እንዲሳተፉ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ በተከታታይ ደም የሚለግሱ የበጎ ፍቃደኛ አደረጃጀቶችን በተሞክሮነት በመውሰድ የበጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች ቁጥር እንዲጨምር እየተደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል። 

ህብረተሰቡ በበጎ ፍቃድ በሚለግሰው ደም የወገኑን ህይወት እየታደገ መሆኑን በመገንዘብ በየሶስት ወሩ ደም የመለገስ ባህሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም