በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ላለፉት ሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የማህበረሰብ ወኪሎች የአጀንዳ ልየታ የምክክር ሂደት ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ላለፉት ሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የማህበረሰብ ወኪሎች የአጀንዳ ልየታ የምክክር ሂደት ተጠናቀቀ
ሶዶ፤ ጥቅምት 20/2017(ኢዜአ):-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ሶዶ ከተማ ላለፉት ሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የማህበረሰብ ወኪሎች የአጀንዳ ልየታ የምክክር ሂደት ተጠናቀቀ።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ ተመራጮች የአጀንዳ ማሰባሰብ የውይይት መድረክ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል።
በሂደቱ ከክልሉ ለአገራዊ የምክክር መድረክ የሚሳተፉና አጀንዳ አደራጅተው የሚያቀርቡ ተወካዮች ተመርጠው ነው ሂደቱ የተጠናቀቀው።
ላለፉት ሶስት ቀናት ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች አጀንዳ ለማደራጀት የሚያስችል ውይይት ሲካሄድ መቆየቱንም ኮሚሽነሩ አውስተዋል።
በዚሁ መሠረት በክልሉ የቅራኔና የግጭት ምንጮች ተብለው የታመኑ መሠረታዊ ችግሮችና ለአገር ይጠቅማሉ ተብለው የተለዩ አጀንዳዎች መለየታቸውን አስረድተዋል።
ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተወከሉ አካላት በአጀንዳዎች ዙሪያ ብዝሃነትን ባማከለና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ በግልጽነት በመወያየት አጀንዳዎቹን መለየታቸውን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
ይህም እንደ አገር ላሉብን ልዩነቶች መፍቻ ቁልፍና ለዴሞክራሲ ግንባታ ትልቅ መሠረት የሚጥል መሆኑን በማከል።
በቀጣይ ባሉት ቀናት የክልሉ ባለድርሻ አካላት ምክክር ቀጥሎ የሚካሄድ መሆኑንም ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ተመራጮቹ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከመንግስት አስፈፃሚ አካላት፣ ከተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ወኪሎች እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማትና የሲቪክ ማህበራት ወኪሎች ጋር በቀጣይ በሚኖረው መድረክ እንደሚሳተፉም ገልጸዋል።