አፍሪካውያን ዘመናዊና ውጤታማ የስታትስቲክስ ስርዓት መገንባት አለባቸው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካውያን ዘመናዊና ውጤታማ የስታትስቲክስ ስርዓት መገንባት አለባቸው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2017(ኢዜአ)፦ አፍሪካውያን ዘመናዊና ውጤታማ የስታትስቲክስ ሥርዓት መገንባት አለባቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።
9ኛው የአፍሪካ ስታትስቲክስ ኮሚሽንና 10ኛው የተባበሩት መንግሥታት ክልላዊ ጂኦ-ስፓሻል መረጃ አስተዳደር ኮሚቴ ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ተጀምሯል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመክፈቻ ንግግራቸው በዛሬው ዓለም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ቢግ ዳታና ዲጂታል ፈጠራዎች ስታትስቲክስ እያንዳንዱን መስክ እየቀየሩ ነው ብለዋል።
እነዚህ ፈጠራዎች የምንመኛትን አፍሪካ ለመፍጠርና እድገትን ለማፋጠን ዕድል እንደሚፈጥሩም ተናግረዋል።
መንግሥታት ዕቅድ ማውጣትንና የውሳኔ አሰጣጥን ለማሻሻል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መቀበል አለባቸው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኑን ገልፀዋል።
አፍሪካ ከልማዳዊ አሠራር፣ የመረጃ አሰባሰብና አጠቃቀም መላቀቅ አለባት ብለዋል።
አህጉሪቱ በዓለም አቀፍ ዲጂታል ኢኮኖሚ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን በፈጠራም መሪ እንድትሆን ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የፖሊሲ ውሳኔዎችን ለማሻሻል የጂኦስፓሻል መረጃዎችንና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን እየተጠቀመች ነው ሲሉ ገልጸዋል።
እነዚህም በርካታ መረጃዎችን በፍጥነትና በትክክል ለመተንተን ያስችሉናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ለምንገነባት መፃኢ አፍሪካ ቁልፍ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድን ጠንካራ በሆነ የመረጃ ሥርዓት አዘጋጅቶ እየተገበረ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ለዕቅድና ክትትል አስፈላጊ መረጃዎችን ለመሰብሰብ እንደ የግብርና ቆጠራና የሥነ-ሕዝብና የጤና ጥናት ያሉ ብሔራዊ ጥናቶችን እናካሂዳለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራን ሙሉ በሙሉ ዲጂታል ለማድረግ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ጠቁመው፤ ስታትስቲክስ አገልግሎታችንን ጥራትና ትክክለኛነት ለማሻሻል ቢግ ዳታና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን እየተጠቀምን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በፈጠራ ችሎታችን ላይ መመሥረቱን ጠቅሰው፤ በጋራ በመሥራት ተግዳሮቶቻችንን ወደ ዕድል መቀየር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በዚህም አካታች ልማትን የሚደግፍና አህጉራዊ ግብን ለማሳካት የሚያግዝ የስታትስቲክስ ምኅዳር መገንባት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአፍሪካ መንግሥታት ዘመናዊና ውጤታማ በሆኑ የስታትስቲክስ ሥርዓቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ የግድ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው ብለዋል።
ለሦስት ቀናት በሚቆየው ጉባዔ በስታትስቲክስ አቅም ግንባታና ሌሎች አጀንዳዎች ዙሪያ ምክክር የሚደረግ ሲሆን፤ የአፍሪካ ኅብረትና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አመራሮች፣ የሀገራት የስታትስቲክስ ተቋማት መሪዎች ተገኝተዋል።