በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2017 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር የሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ባህር ዳር ከተማ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 10 ላይ በድሬዳዋ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ባህር ዳር ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል።
ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ሶስት ግቦችን አስተናግዷል።
በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ባህር ዳር ከተማ በስድስት ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሲዳማ ቡና በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች አራቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል።
በጨዋታዎቹ ቡድኑ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለት ግቦችን አስተናግዷል።
በዘላለም ሽፈራው የሚሰለጥነው ሲዳማ ቡና 12 ነጥብ የአንደኝነቱን ደረጃ ይዟል።
ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ሀዲያ ሆሳዕና ከወላይታ ድቻ ይጫወታሉ።
ሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በጨዋታዎቹ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አራት ግቦችን አስተናግዷል።
በግርማ ታደሰ የሚመራው ሀዲያ ሆሳዕና በአራት ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ወላይታ ድቻ በሊጉ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል።
ቡድኑ በጨዋታዎቹ ስምንት ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ጎሎችን አስተናግዷል።
በያሬድ ገመቹ የሚሰለጥነው ወላይታ ድቻ በዘጠኝ ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የስድስተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ኢትዮጵያ መድን ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን እንዲሁም አርባምንጭ ከተማ ፋሲል ከነማን በተመሳሳይ 1 ለ 0 አሸንፈዋል።