ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች መደበኛውን የፍትህ ስርዓት በማገዝ ህብረተሰቡ በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኝ እያደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች መደበኛውን የፍትህ ስርዓት በማገዝ ህብረተሰቡ በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኝ እያደረጉ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2017(ኢዜአ)፦ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች መደበኛውን የፍትህ ስርዓት በማገዝ ህብረተሰቡ በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኝ እያደረጉ መሆኑን ፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) ተናገሩ።
በኦሮሚያ ክልል ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ትግበራ የህግ ተፅእኖ ግምገማ ጥናት ሪፖርት ይፋ ተደርጓል፡፡
በጥናቱም በኦሮሚያ ክልል ተግባራዊ የተደረገው የኦሮሚያ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ህብረተሰቡን በቅርበት እያገለገሉ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ባህላዊ እና ልማዳዊ የግጭት አፈታትን ዘዴዎችን በማካተት የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዲርጊት መርሃግብር ተግባራዊ ለማድረግ የተከናወኑ ስራዎች ውጤት እያስገኙ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሚኒስቴሩ የሶስት ዓመት የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን የድርጊት መርኃ ግብር አዘጋጅቶ መተግበር ከጀመረ አንድ ዓመት ማስቆጠሩንም ጠቁመዋል።
ይህም መደበኛ ፍርድ ቤቶችን በማገዝ በኩል ከፍተኛ አስተዋዕጾ አለው ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ገዛሊ አባሲመል በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል በ2016 ዓም ከ480 ሺህ በላይ መዛግብት ለባህላዊ ፍርድ ቤቶች ቀርበው አብዛኞቹ እልባት እንደተሰጣቸው አስታውቀዋል።
በክልሉ 6 ሺህ 300 ቀበሌዎች ባህላዊ ፍርድ ቤቶች መቋቋማቸውን ገልጸው በቀጣይ ተግባሩ በሁሉም ቀበሌዎች እንደሚስፋፋም ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ የመሬት ፍትህ አመላካች ሰነድ ተመርቋል።
ሰነዱ የፍትህ ሚኒስቴር ከሄግ ኢኖቬሽን የህግ ተቋም ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀውና ከመሬት ጋር የተያያዙ ግጭቶችን ለመፍታት የሚያስችል ልምድና ተሞክሮን የያዘ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) በአገሪቱ መሬት ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባለፈ የማንነትና የባህል ጉዳይ በመሆኑ ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶች የባለቤትነት፣ የውርስ፣ የወሰን፣ የግጦሽና ጉዳዮችን የሚመለከቱ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህንንም ክፍተት ለመሙላትና በጥናት ለመመለስ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ጥናት ተደርጎ የኢትዮጵያ ፍትሃዊ የመሬት አስተዳደር መመሪያ መውጣቱን ጠቁመዋል።
መንግስት በመሬት ዙሪያ ያወጣው አዋጅ ተግባራዊ ሲደረግ በአፈጻጸም ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ከመውሰድ ይልቅ በባህላዊ ፍርድ ቤቶች ሊፈቱ ይችላሉ ብለዋል።
የሄግ ኢኖቬሽን የህግ ተቋም ዋና ስራ አስፈፃሚ ሳሙኤል ሙለር (ዶ/ር ) በበኩላቸው ሰነዱ በመሬት ላይ የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችሉና በመሬት ፍትህ አስተዳደር ውስጥ ያሉ ተዋንያን ሊጠቀሙበት የሚችሉበት እንደሆነ ጠቁመዋል።
ሰነዱ የኢትየጵያ የመሬት ፍትህ ለሁሉም ፍትሃዊ፣ ዘላቂ እና ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።