ቀጥታ፡

በክልሉ ለአገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ  ዝግጅት መጠናቀቁን ኮሚሽኑ አስታወቀ

ቦንጋ፤ ጥቅምት 19/2017(ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ  ለሚካሄደው የአገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን  የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የአጀንዳ ቀረፃ እና ምክክር አስተባባሪ አቶ ተመስገን አብዲሳ  እንዳመለከቱት፤  ኮሚሽኑ አሳታፊነትና አካታችነትን መሠረት ባደረገ መልኩ የተሳታፊዎች ልየታን በአገሪቱ 10 ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች አከናውኗል።

የተሳታፊዎች ልየታውም በወረዳ ደረጃ ሴቶች፣ወጣቶች እና መምህራንን ጨምሮ 10 የህብረተሰብ ክፍሎችን እንዲሁም በክልል ደረጃ የተለያዩ ተቋማትንና ሲቪክ ማህበራትን  ያካተተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ኮሚሽኑ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ስራ እያከናወነ መሆኑንም አስተባባሪው አቶ ተመስገን አብዲሳ አስረድተዋል።

አሁን ላይ ኮሚሽኑ በተለያዩ ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረኮችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ከጥቅምት 24/  2017 ዓ.ም  ጀምሮ  በደቡብ ምዕራብ ኢትዮዽያ ሕዝቦች ክልል በተመሳሳይ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማጠናቀቁንም አስታውቀዋል። 

በመርሃ ግብሩም በሁለት ምዕራፍ ተከፋፍሎ እንደሚካሄድ  የገለጹት አቶ ተመስገን፤  የአጀንዳ ማሰባሰብና የአገራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎች ምርጫም እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

ከጥቅምት 24/2017 ዓ.ም ጀምሮ በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ከ57 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተመረጡ 1ሺህ 140 የህብረተሰብ ወኪሎች እንደሚሳተፉም  ገልጸዋል።

መርሃ ግብሩ በክልሉ በቦንጋ ከተማ በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ለ7 ተከታታይ ቀናት  እንደሚቆይ አብራርተዋል።

ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ ሁለንተናዊ ሰላምና እድገት ትርጉም ያለው አገራዊ የምክክር ዓላማ እንዲሳካ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም አቶ ተመስገን አብዲሳ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም