ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ፈቺ ትውልድን የማፍራት ተግባራቸውን እንዲያጠናክሩ በትኩረት እየተሰራ ነው - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

ዲላ፤ጥቅምት 19/2017(ኢዜአ):- ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ጥረትን ጠብቀው ችግር ፈቺ ትውልድን የማፍራት ተግባራቸውን እንዲያጠናክሩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

ሚኒስትሩ በትምህርት ጥራትና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚና ዙሪያ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ስራተኞች ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

በዚህ ወቅት ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የህብረተሰቡን ችግርና ፍላጎት በመለየት የመፍትሄ ሃሳብ የማመንጨት ተግባራቸውን ማጠናከር አለባቸው።

ተቋማቱ የውስጥ ችግሮቻቸውን ከመፍታት በተጓዳኝ እንደ ሀገር ማሰብ እንደ ዓለም አቀፍ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በተለይ ተቋማቱ የእውቀትና የእውነት ማዕከል ብቻ እንዲሆኑ ምሁራን በጥናትና ምርምር የተደገፈ ውጤታማ ስራ ማከናወን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የዩኒቨርሲቲዎችን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ተሳትፎ ማጠናከር የመድረኩ ዓላማ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ጥራትን ጠብቀው የሀገር ችግር ፈቺ ትውልድን የማፍራት ተግባራቸውን እንዲያጠናክሩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን በማጠናከርም ለነገው ትውልድ የተሻለ ሀገር ለማውረስ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ተወዳዳሪነቱን ለማስፋት ከሀገር ውስጥና ከውጭ የምርምር ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤልያስ አለሙ ናቸው።


 

ዩኒቨርሲቲው ያለውን የተደራጀ ቤተ ሙከራ ጨምሮ የሰውና የግብዓት ሃብትና አቅሙን በአግባቡ በመጠቀም የትምህርት ስርዓቱን ለማዘመን እየሰራ ነው ብለዋል።

ምሁራን ያላቸውን እውቀትና ጊዜ ለተቋም ለውጥ በመስጠት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ገልጸዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ አባል ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ምሁራን አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይ በማህበር ለተደራጁ መምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው መምህራን ናቸው ያሉት ደግሞ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በዩኒቨርሲቲው የግብርና ምጣኔ መምህርና ተመራማሪ ጠብባ ሐሰን(ዶ/ር) ናቸው።

በውይይት መድረኩ የጌዴኦ ዞንና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም