ቅርሶችን መመደብና ማስተዳደር የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ እየተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቅርሶችን መመደብና ማስተዳደር የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ እየተዘጋጀ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2017(ኢዜአ)፦ ቅርሶችን በብሔራዊና በክልል ደረጃ መመደብና ማስተዳደር የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን በ2016 አፈጻጸም እና በ2017 ዕቅድ ዙሪያ "የተግባርና አስተሳሰብ አንድነት ለላቀ ስኬት" በሚል መሪ ሃሳብ ምክክር አካሂዷል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው በዚህ ወቅት፤ ቅርሶች በታሪካዊ ምስክርነታቸውና በሀገር ሃብትነታቸው ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተጠብቀው እንዲተላለፉ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ቅርሶቹን በሳይንሳዊ መንገድ ከመመዝገብ ጀምሮ የተመዘገቡትን የመከታተል፣ የመንከባከብና የማልማት ስራ ላይ ትኩረት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
ከለውጡ ወዲህ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ በሰጠው ትኩረት ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች ከትውፊታዊ ማስረጃነታቸው ባለፈ ለኢኮኖሚያዊ ጥቅም መዋል መጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡
ባለስልጣኑ በ2016 ዓ.ም 8 ሺህ 334 ተንቀሳቃሽ እና 1 ሺህ 328 ቋሚ ቅርሶችን በብሔራዊና በክልል ደረጃ መመዝገቡን በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ሶስት የሚዳሰሱና አንድ የማይዳሰስ ቅርስ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት( ዩኔስኮ) ማስመዝገብ የተቻለበት ስኬታማ ዓመት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተለያዩ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ባለቤት እንደመሆኗ መጠን ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስመዝገብ፣ የማጥናትና የመጠበቅ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
በቀጣይም ቅርሶችን በብሔራዊ እና በክልል ቅርስነት መመደብ የሚያስችልና የሙዚዬም ደረጃ ምደባና እውቅና አሰጣጥ ፖሊሲ ማዘጋጀት የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ረቂቅ መመሪያው ብሔራዊ ጥቅም ያላቸው ቅርሶች በቅርስ ባለስልጣን ስር መተዳደር እንዲችሉ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
መመሪያው ባህላዊ ይዘት ያላቸውን ቅርሶች ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ መዋቅሮች የራሳቸውን ሙዚዬም በማዘጋጀት ቅርሶቹን መጠበቅ፣ መንከባከብና መሰነድ የሚያስችላቸው ነው ብለዋል፡፡
ይህም የቅርስ አስተዳደር ስራውን ከማቅለል ባሻገር ቅርሶች እንዲጠበቁ ምቹ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ መድረኩ ጠንካራ አፈጻጸማችንን እንድናስቀጥልና ድክመቶቻችንን እንድንቀርፍ ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር በጋራ እንድንሰራ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
መድረኩ በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑን የጋምቤላ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ፔል ፒተር ተናግረዋል፡፡