የፖሊሲ ማስተግበሪያ ስትራቴጂው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅምን በመጠቀም አለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ያሳድጋል - ኢዜአ አማርኛ
የፖሊሲ ማስተግበሪያ ስትራቴጂው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅምን በመጠቀም አለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ያሳድጋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2017(ኢዜአ)፦ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ማስተግበሪያ ስትራቴጂ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅምን በመጠቀም የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥና አለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እንደሚያሳድግ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከፈረንጆቹ 2025 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ማስተግበሪያ ስትራቴጂ በቅርቡ ይጸድቃል ተብሏል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት አለም አቀፍ የንግድ ማዕከል ጋር በመተባበር ለፖሊሲ ማስተግበሪያ ስትራቴጂው ግብዓት ለማሰባሰብ ያለመ አውደ ጥናት አካሂዷል።
በዚህ ወቅት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ፖሊሲው ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ የተያዘውን አገራዊ ስትራቴጂ ለማሳካት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የፖሊሲ ማስተግበሪያ ስትራቴጂው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅምን በመጠቀም የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
በሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ጥቅም ላይ የዋሉ ቴክኖሎጂዎች ለውጥ ለማምጣት ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው ጠቅሰዋል፡፡
በሚኒስቴሩ የኢኖቬሽን አማካሪ ዶክተር ሰለሞን በላይ ከዚህ ቀደም የነበረው ፖሊሲ ለግሉ ዘርፍ ትኩረት ያልሰጠና የአስተዳደር ስርዓቱም በህግ ያልተደገፈ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ይህን ተከትሎ በ2014 ዓ.ም እነዚህን ጉዳዮች ታሳቢ ባደረገ መልኩ ፖሊሲው መፅደቁን ተናግረዋል።
ፖሊሲው የስታርትአፖችና ኢንተርፕራይዞች ተወዳዳሪነትና ዲጂታላይዜሽን እንዲሁም የፋይናንስ አቅርቦትን በተመለከተ ዝርዝር ሁኔታዎችን በማካተት የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።
ፖሊሲውን ለማስፈፀም ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ውይይት ሲደረግበት መቆየቱን አንስተው በዛሬው እለትም ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት የግብዓት ማሰባሰቢያ አውደ ጥናት መካሄዱን አስረድተዋል።
ስትራቴጂው አስፈላጊው ማስተካከያ ተደርጎበት ከፈረንጆቹ 2025 ጀምሮ ለአስር አመታት ተግባራዊ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
በአፍሪካ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ አዘጋጅተው ወደ ትግበራ የገቡት ጥቂት አገራት እንደሆኑ የገለፁት ደግሞ የተባበሩት መንግስታት አለም አቀፍ የንግድ ማዕከል የኢትዮጵያ አስተባባሪ ሳሙኤል ፈረደ ናቸው።
በኢትዮጵያም ፖሊሲውን በአግባቡ በመተግበር ውጤታማ ስራ ለማከናወን ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።