የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ኢትዮጵያ በዲጂታል ልማት እያደረገች ያለችውን ጥረት እንደሚደግፍ ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ኢትዮጵያ በዲጂታል ልማት እያደረገች ያለችውን ጥረት እንደሚደግፍ ገለፀ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2017(ኢዜአ)፦የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) ኢትዮጵያ በዲጂታል ልማት እያከናወነች ያለው ተግባር የሚበረታታና የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታወቀ።
በኢትዮጵያ የኮይካ ዳይሬክተር ሀን ዲዮግ ቾ ለኢዜአ እንዳሉት ኮይካ ከኢትዮጵያ ጋር በአራት የልማት ትብብር መስኮች እየሰራ ይገኛል።
የአምራች ዘርፉን አቅም ማሳደግ፣ የጤናውን ዘርፍ፣ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረትና አካታች ልማት ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ ገልፀዋል።
ኮይካ በዲጂታል ዘርፉም ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት አሰጣጥን እየደገፈ መሆኑን አንስተዋል።
በአይሲቲ ዘርፍ ያሉ ስታርትአፖችን በአቅም ግንባታና በገንዘብ እየደገፉ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስና ስትራይድ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ መርሃግብሮች በኢትዮጵያ ያለውን የዲጅታል ትውልድ ግንባታ የሚያፋጥኑ ናቸው ብለዋል።
ባለንበት ዘመን ኢኮኖሚን ለማሳደግና ማህበረሰብን ለማበልፀግ ዲጂታል እውቀት የግድ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ መንግስት ዲጂታላይዜሽን ላይ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ እንደሆነ ገልጸዋል።
ኮይካም ከኢትዮጵያ ጋር በዲጂታል ዘርፉ በትብብር እየሰራ በመሆኑም ኩራት ይሰማዋል ነው ያሉት።
በእያንዳንዱ የልማት ትብብሮች የተለያዩ መርሃግብሮች እየተከናወኑ መሆናቸውን አንስተው ለእነዚህ መርሃግብሮች 150 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በጀት መመደቡንም ተናግረዋል።
ከተያዘው በጀት በየዓመቱ እስከ 40 ሚሊየን ዶላር የሚመደብ ሲሆን ለተያዘው ዓመትም 35 ሚሊየን ዶላር እንደተመደበ ገልፀዋል።
በግብርናው ዘርፍ የወተት ምርት ጥራት ማስጠበቅ የሚያስችል የ10 ሚሊየን ዶላር መርሃግብር እየተተገበረ መሆኑን አንስተው እ.አ.አ በ2026 ተመሳሳይ የ10 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።