23ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሺዬቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
23ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሺዬቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2017(ኢዜአ)፦23ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሺዬቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ እ.አ.አ በየካቲት ወር 2025 በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ ተካሄዷል።
ከዓመታዊ ስብሰባው ጎን ለጎን 22ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሺዬቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ ተደርጓል።
በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የተመራው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በስብሰባው ላይ ተሳትፎ አድርጓል።
ስብሰባው ላይ 23ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሺዬቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ እ.አ.አ በየካቲት ወር 2025 በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ይፋ ሆኗል።
ኢኒሺቴቩ እስከ አሁን ያስመዘገባቸው ስኬቶች እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ምክክር እንደሚደረግ ተገልጿል።
በመሰረተ ልማት፣ ንግድን በማሳለጥ፣ ኢንቨስትመንት፣ የሰው ኃይል ልማት እና አገራት የማይበገር አቅም በመገንባት የኢኮኖሚ ትስስርን ማጠናከር እና የኢኒሼቲቩን ተጽእኖ ፈጣሪነት ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት ኢትዮጵያ እያከናወነች የምትገኘውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ አስመልክቶ ስብሰባው እና በሁለትዮሽ ውይይቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሩ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ለኢትዮጵያ እና ሌሎች በማደግ ላይ ለሚገኙ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል፣የኢኮኖሚ እና የልማት ስራዎች የሚያደርጉትን የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያሳድጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በስብሰባው ላይ የአፍሪካ የፋይናንስ ሚኒስትሮች፣የልማት አጋሮች፣ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ እ.አ.አ በ2019 የተቋቋመ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የኢኒሼቲቩ አባል አገራት ናቸው።
ኢኒሼቲቩ ንግድ እና ኢኮኖሚን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያለውን ቀጣናዊ ትብብር ማጠናከር ዋንኛ አላማው አድርጓል።
እስከ አሁን ድረስ 11 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ሀብት ኢኒሼቲቩ ሊያሳካቸው ላቀዳቸው ግቦች መሰብሰቡን መረጃዎች ያመለክታሉ።